የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ሥራ ማኅበር ተመሠረተ፡፡

247

ባሕር ዳር፡ መስከረም 18/213ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ሥራ ማኅበር መመሥረቱን አስታውቋል፡፡

ማኅበሩ በይፋ መመሥረቱን ተከትሎ በቀጣይ ሊሠራቸው ያሰባቸው ተግባራትን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው ማኅበሩ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ተመዝግቦ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ሕጋዊ ሰውነት እንደተሰጠው ገልጿል።

ማኅበሩ የማስታወቂያ ሥራዎችን በመከታተል ብሎም በኢትዮጵያ የማስታወቂያ ሥራ እንዲጎለብትና ወደ ኢንዱስትሪነት እንዲያድግ ለማስቻል ትኩረት አድርጎ የሚሠራ መሆኑም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ሥራ ማኅበር ፕሬዝዳንት አለባቸው ወዳይ እንደገለጹት በማስታወቂያ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን አጥንቶ በማውጣት እንዲፈቱ ማድረግ የማኅበሩ ቀዳሚ ተግባር ነው።
“የማስታወቂያ ድርጅቶችን በማቀፍ የተቋቋመው ይህ ማኅበር ከዚህ ቀደም ችግሮችን በተናጠል ለመፍታት ይደረግ የነበረው ጥረት እምብዛም ውጤታማ ባለመሆኑ መሰባሰብና መደራጀቱ የመደመጥ ሁኔታን ከፍ ለማድረግ ያስችላል” ብለዋል።

በቀጣይ ጥራት ያላቸው የማስታወቂያ ሥራዎች እንዲሠሩና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ጥቅም እንዲከበር ለማድረግ ማኅበሩ የራሱን ሚና እንደሚወጣ ፕሬዝዳንቱ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአገሪቱን ባህልና እሴት የጠበቁ የማስታወቂያ ሥራዎች ለሕዝብ እንዲቀርቡ እንደሚያደርግና ከማስታወቂያ ፖሊሲ አንጻር ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ማኅበሩ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሠራም አቶ አለባቸው ተናግረዋል።

“ማኅበሩ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለተቸገሩ ሰዎች በዘመን መለወጫ በዓል ከ250 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለበዓል የሚሆኑ ቁሶችን ድጋፍ አድርጓል” ብለዋል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ለግንዛቤ ማስጨበጫ የሚያገለግሉ የቢልቦርድ ማስታወቂያዎችን በተለያዩ አካባቢዎች በመስቀል አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

Previous articleማን ይሁን አርአያ?
Next articleበሎንደን የሚኖሩ የወልድያና አካባቢዋ ነዋሪዎች ለኮሮናቫይረስ ሕክምና አገልግሎት የሚዉል ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡