
ባሕር ዳር፡ መስከረም 18/213ዓ.ም (አብመድ) ያሁኑ ይባስ ! ከጽሕፈት ቤቶች አጥር በር ላይ እኔና የሥራ ባልደረባዬ ለመግባት ሁለት የወረዳው አመራሮች ደግሞ ለመውጣት መግቢያው ላይ ተገናኝተናል። አንደኛው አመራር ግን “ባክህ ኮሮና የለም ምናባቱ” በማለት የሥራ ባልደረባዬን አንገት አቅፎ ይስመው ጀመር። ጓደኛየም እየተገላበጠ ተሳመ የሚገርመው ደግሞ ኮሮና የለም እያለ የሚስመው የወረዳው ጤና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ መሆኑ ነው።
በእርግጥ ኃላፊነት አልባ የሆኑ ኃላፊዎች የሀገርን ምሰሶ ይንዳሉ የሚባለው እውነት ነው። “ኮሮና ገዳይ ነውና መሸፋፈን፣ መራራቅንና መታጠብን አትርሱ” እያለ የሚያላዝን አስተማሪ እንዲህ በአደባባይ ሲተቃቀፍ ልብ ብሎ ያየ ተመልካች ምን እንደሚማር ለእናንተ ማውጋት ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል።
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል አንዷ በሆነችው ጃዊ ወረዳ ተገኝተናል። ሰዓቱ ከቀኑ ስምንት ሰዓት መሆኑ ከአካባቢው በርሃ ጋር ተዳምሮ ሙቀቱ እጅግ አይሏል! ሰውነትን ይወብቅም ይዟል።
ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ ነው እንደ ወፍ ስትከንፍ በነበረችው ሀይሩፍ መኪና ታግዤ ጃዊ ወረዳ የደረስኩት። የተገኘውን እንደ ነገሩ ቀማምሼ ለሌላ ተልኮ እዚህ በሥራ ላይ ከነበረው የሥራ ባልደረባዬ ጋር ለሥራ የሚያግዙንን ቁሶች ይዘን ወደ ጽሕፈት ቤቶች ዘልቀናል። በዚህ ወቅት ነበር ያስደነገጠኝንም ያስገረመኝንም ክስተት ከምክትል ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ድርጊት የታዘብኩት።
ከፊት ሆኖ ዕራዩን እየተከተለ የሚሄድ መሪ ከጠፋ የሕዝቡ መዘናጋትና መረንነት ብዙ ላይደንቅ ይችላል። ግን በእጅጉ ሊታሰብበትና ሊታረም የሚገባው ይመስለኛል።
በማለዳ ነው ባሕር ዳር አውቶብስ መናኸሪያ የተገኘሁት፤ በመናኸሪያው ከአስተናጋጆች ጀምሮ አብዛኛው ሰው የአፍና የፍንጫ መሸፈኛ አድርጓል። ተሳፋሪው ግን እምብዛም አለበሰም፤ መኪናው ሞልቶ መንቀሳቀስ ስንጀምር የመኪናው ረዳት ለሁሉም መመሪያ በሚመስል መልኩ የፊት መሸፈኛችንን እንድናደርግ ማሳሰብ ጀመረ ልብ ብሎ ትኩረት የሰጠው ግን አልነበረም።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ባሕር ዳር መውጫ ኬላ ላይ ልዩ ኃይሎች አካባቢ ስንደርስ ረዳቱ ልመና በሚመስል መንገድ ‘‘እባካችሁ ፖሊሶች መጥተዋል ልበሱ’’ ብሎ ወደ ፖሊሶች ተጠግቶ መኪናው ቆመ። በዚህ ቅፅበት ወንዶች ከኪሳቸው ሴቶችም ከቦርሳቸውና ከጉያቸው እያወጡ የፊት ማስካቸውን ለበሱ። ወዲያውም የክልሉን የልዩ ኃይል ልብስ የለበሱ የእጅ ጎንት ያጠለቁ የፊት መሸፈኛ ግን ያላደረጉ የፀጥታ ኃይሎች ሁሉም እንዲወጡ አዝዘው መኪናውንና ከውስጥ ያሉትን ሻንጣዎች ፈትሸው በመቀጠል ሰውንም እየፈተሹ አስገብተው መኪናው ጉዞውን እንዲቀጥል ፍቃድ ሰጥተውታል።
የዚህ ዓይነት ተደጋጋሚ ክስተት በየቅርብ ርቀት ይደጋገማል ተሳፍሪውም “ማስክህን አድርግ አላደርግም” ድብብቆሽ ዓይነት ጨዋታ ነፍሱንና ጤናውን አስይዞ የሚጫወት ይመስላል። ፈታሽ ሲመጣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛውን ከመቅፅበት ያደርገዋል፤ ፈታሽ ሳይኖር እንደ ዱምቡሎ ሳንቲም ወደ ኪሱ ይወረውረዋል። በርግጥ ፈታሽ የፀጥታ ኃይሎችም ልበሱ እንጅ ለብሰው አይታዩም አመራሩም እንደዛው ታዲያ አርአያ ሆኖ የሚመራ በሌለበት መዘናጋቱን እንዴት በሕዝቡ መፍረድ ይቻላል?
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ብዙ እየተጓዝን እንደየሁኔታው የደንብ ልብስ የለበሱ ወጣቶችም መኪናውን አስቁመው ለግንባታ የዕርዳታ መዋጮ ይጠይቃሉ። በመሀሉም የተቀቀለ ሽንብራ ‘‘በረከቱ ይድረሳችሁ!’’ እያሉ በየፊታችን ያዞራሉ። ብዙ ነገር ሲነካካ በነበረው ባልታጠቡ እጆች ከጥሬው እያነሱ ይቋደሳሉ፤ “ኧረ አልታጠብኩም ብዙ ነገር ነክቻለሁ “የሚል የለም በዚህ መሀል ግን የኮሮናቫይረስ መተላለፊያ መንገዱን ድንገት ያለመረዳት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ገመትኩ።
ከባሕር ዳር ተነስቼ በጃግኒ ዙሬ ጃዊ እስክገባ በሁሉም ከተሞች ኮሮና ያለ አይመስልም መዘናጋቱ እጅግ በዝቷል። የፊት መሸፈኛ የሚጠቀም የለም፤ ማኅበራዊ ርቀት የሚታሰብ አይደለም፤ ምን አለፋችሁ ሰው ተቃቅፎና ተዛዝሎ ነው የሚውለው ማለት ይቻላል።
ጃዊ ወረዳም ለምሳሌ የሚሆን ማስክ ያደረገ ሰው በዓይኔ ሳማትርም አላገኘሁም፤ ማስክ የሚያደርግ ሰውን የሚፈልገው ዓይኔ ያሻውን ሳያገኝ ባንድ ሰብሰብ ብለው ወደ ሚገኙት ጽሕፈት ቤቶች ዘለቅሁ፤ ማስክ ያደረገ የለም።
ግን ለምን ይሆን የተማረው የመንግሥት ሠራተኛውም ሆነ ኅብረተሰቡን የሚመራው አመራር የኮሮናቫይረስን በመከላከል አርአያ ሆኖ ፊት በመቆም መምራት የተሳነው? መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ ነው።
በነገታው ወደ ገጠር ቀበሌ ወጣ ለማለት መናኸሪያ መኪና ይዘናል፤ መኪናዋ ሚኒባስ ናት፤ የመያዝ ልኳ እርግጠኛ ባልሆንም ከአሥራ አራት አይበልጥም፤ ነገር ግን በሰው ላይ ሰው ደርባ 22 ሰው ይዛ ጉዞዋን ጀምራለች። በመኪናው ውስጥ ካለነው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ያደረግነው እኔና የኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ባለሙያ ብቻ ነን። ሌላው ሌጣውን ሆኖ ነው አፍ ለአፍ ገጥሞ የሚያወጋው። በመኪናው ውስጥ በተደጋጋሚ የሚስሉትንም ታዝቢያለሁ።
ኮሮናን የተመለከተ የግንዛቤ እጥረት አለ ብየ ስላሰብኩ ከአርሶ አደሮች ጋር ጥቂት ሐሳብ ተለዋዋወጥኩ። አርሶ አደር አለነ ስሜ ይባላሉ፤ ስለኮሮና ቫይረስ በቂ ግንዛቤ አላቸው፡፡ ስለመከላከያውም አፍና አፍንጫን መሸፈን መታጠብ እና አለመቀራረብ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ታዲያ አሁን ለምን ባንድ ተሰበሰባችሁ? ስል ጥያቄ አነሳሁ፤ እሳቸውም “ሥራ ላይ ስለሆንን ነው፤ ደሞ እኛ በአንድ ቀየ ያለነው እንተማመናለን፤ ለዛ ነው፡፡ እንግዳ ሰው ሲመጣ አንቀርብም” በማለት ገለፁልኝ። ደሞም በርሃው ላይ በሽታው ያው አቅም የለውም ስለሚባል ኅብረተሰብ አልፈራውም በማለትም አስረዱኝ፤ እርሳቸው ግን ይህንን አያምኑበትም።
አቶ ወሰን ትዛዙ በጃዊ ወረዳ አስተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት ውስጥ የጤና ኦፊሰር ናቸው። በወረዳው ያለው መዘናጋት አሳሳቢ እንደሆነ ይገልፃሉ። የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎቾ በተገኙ ጊዜ ኅብረተሰቡም ሆነ የመከላከል ግብረ ኃይሉ ከፍተኛ ርብርብ አድርጎ ነበር፤ የሰውም ትኩረትና ጥንቃቄውም አበረታች እንደነበረ ያስረዳሉ።
‘‘ዛሬ ላይ ኅብረተሰቡ ብቻ አይደለም አመራሩና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይሉ እራሱም ቫይረሱን እየተከላከለ ለሌላው አርአያ መሆን አልቻለም። በዚህ ምክንያት በወረዳው በሚያስፈራ መልኩ መዘናጋት ይታያል’’ በማለት ይገልፃሉ። በዚህ ከቀጠለም ሁኔታው ነገ ላይ የከፋ ችግር መፍጠሩ አይቀርምና በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
የጃዊ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንዷለም አብዩ በበኩላቸው በሽታው ወደ ሀገራችን በገባበት ወቅት በወረዳው ኮሚቴ አቋቁመው ግንዛቤ ከመፍጠር በዘለለ እህልን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን የማሰባሰብ እንዲሁም ማቆያወችን የማደራጀት ስራ ከዚያም አልፎ አንቡላሶችንም ዝግጁ የማድረግ ስራ መሰራቱን ያስታውሳሉ።
‘‘እስከ ቅርብ ጊዜ የኮሮናቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይሉ ያከናወናቸው ተግባራት እየቀረቡ ሲገመግሙና በአግባቡ ሲመሩ ነበር’’ የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መቀዛቀዝ በመታየቱ መዘናጋቱ ጨምሯል ይላሉ። ‘‘ይህንንም በቅርብ ተነጋግረን የማሻሻል ሥራ መሠራት አለበት’’ ብለው እንደሚያምኑም አስረድተዋል።
በርግጥ በአሁኑ ወቅቱ በሁሉም በሚባል አካባቢ ለኮሮናቫይረስ የሚሰጠው ትኩረት እጅግ ተቀዛቅዟል፤ መዘናጋቱም በዝቷል። አሁን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ትምህርት ሲከፈት የከፋ ችግር ሊፈጠር ይችላልና አሁን ላይ የቀደመውን ትኩረት በመመለስና ህብረተሰቡን የማንቃት ሥራ ላይ መረባረብ ይገባል።
በኩር (ግርማ ሙሉጌታ) መስከረም 18 ቀን 2013 ዓ.ም ዕትም