ባሕር ዳር፡ ጳጉሜን 2/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ስነ ሥርዓት በባሕር ዳር ከተማ እየተከበረ ነው፡፡
በስነስርዓቱ የአማራ ክልል ህዝብ ለህግ የበላይነት መጠበቅ፣ ለሰላማዊ ግንኙነት እና ለሰላም ልዕልና ሕይወቱን መገበሩን የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን በገነባት ሀገር ዜጎች በማንነታቸው በደል እንዳይደርስባቸውም በመሻት በጽኑ መታገሉንም ገልጸዋል፡፡ የጸረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ተወግዶ ለውጥ እንዲመጣ በተደረገው ትግል የአማራ ክልል ሕዝብ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረውም አስታውሰዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ሊመለሱለት የሚገባቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች በጥበብ እና በሠላማዊ መንገድ ብቻ እንዲመለስ እንደሚያምንም ተናግረዋል፡፡ ሀሰተኛ እና የተዛቡ ትርክቶች እንዲታረሙ፣ የኢኮኖሚ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ ሕገ-መንግስት እንዲሻሻል፣ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች እንዲመለሱ እና ሀቀኛ ፌደራሊዝም እንዲተገበር የሕዝቡ መሠረታዊ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ አቶ ግዛቸው ጥያቄዎቹ “ወደ ብልጽግና ለሚደረገው ጉዞ መሳካት ሁነኛ መታገያ አጀንዳዎች ናቸው” ብለዋል፡፡
እነዚህን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የሰላም መስፈን እና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ለውጡን ተከትሎ ስልጣን የተቀማው አኩራፊ ቡድን ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን የሕዝብ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ ክልሉን የብጥብጥ ቀጣና ለማድረግ የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርግ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡ በዚህም የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል፣ ከሀብት ንብረታቸው እና ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ በርካታ ንብረትም ወድሟል፡፡
ይሁን እንጂ የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ለሰላም መስፈን እና ለሕግ የበላይነት መከበር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ ክልሉን እና ሀገረ መንግሥቱን የማተራመስ ዓላማው መክሸፉን አመላክተዋል፡፡ መንግሥትና ሕዝብ ጠንካራ አቋም ይዘው መንቀሳቀሳቸው አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ ተግባሩ ወደፊት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው አቶ ግዛቸው የተናገሩት፡፡
የክልሉ መንግሥት ጳጉሜን በተለያዩ መርሀ ግብሮች ሰይሞ እያከበረ ነው፡፡ ዛሬ ጳጉሜን 2/2012 ዓ.ም ደግሞ የሰላም ቀን ተብሎ ተሰይሟል። በአማራ ክልል አንጻራዊ ለሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ ለነበራቸው አካላት የክልሉ መንግሥት ዛሬ እውቅና ይሰጣል።
ቀኑም የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአጎራባች ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የክልል እና የዞን የሥራ ኃላፊዎች እና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት በባሕር ዳር ከተማ እየተከበረ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ