ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 27/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች በአዋሽ ተፋሰስ በሚገኙ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ማጋጠሙን የአዋሽ ተፋሰስ ልማት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ዳዋ ኢሉ ወረዳ፣ ምዕራብ ሸዋ ዞን ከፊል ኤጄሬ ወረዳ፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ቦራ፣ አዳማ፣ ከፊል ፈንታሌ ወረዳዎች እና መተሃራ ከተማ የጎርፍ አደጋው አጋጥሟል።
በተመሳሳይ በአፋር ክልል አሚበራ ወረዳ፣ አሳኢታ፣ ዱብቲ፣ ገለአሉ፣ ገዋኔ እና አፋምቦ ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ ማጋጠሙን የአዋሽ ተፋሰስ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበጀ መንገሻ ለፋብኮ ገልፀዋል።
በአካባቢዎቹ የጎርፍ አደጋው ከመከሰቱ አስቀድሞ ለመከላከል በበጋ ወራት የወንዙን የመሸከም አቅም የማስፋት ስራዎች እና የጎርፍ መከላከያ ግንባታዎች መከናወናቸው ነው የተነገረው።
በክረምቱ ወቅትም በሰው ሃይል ጭምር የመከላከል ስራ ሲሰራ ቢቆይም የክረምቱ ዝናብ ክብደት እያየለ በመምጣቱ እና የግድቦች የውሃ ሙሌት ከአቅም በላይ መሆኑን ተከትሎ በተፋሰሱ በሚገኙ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ እየተከሰተ መሆኑ ተነግሯል።
ዛሬ ካጋጠመው የጎርፍ አደጋ ለሚወጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል።
የጎርፍ አደጋው ከተከሰተ በኋላ በቅድሚያ የሰው ሕይወት የማዳን ስራ ከክልሎች ብሎ ከዞን እና ወረዳ አመራሮች ጋር እየተከናወነ ይገኛል ተብሏል።
የክረምቱ የዝናብ ክብደት አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሜቴዎሮሎጂ መረጃዎች እንደሚያመለክቱ የገለፁት ኃላፊው በአዋሽ ወንዝ ገባሮች እና በዋናው በአዋሽ ወንዝ የሚገኙ ዜጎችን ከአካባቢዎቹ ማውጣት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በጎርፍ ምክንያት ከአካባቢዎቹ ለተፈናቀሉ ዜጎችም የክልል መንግስታት እና የፌዴራል መንግስታት ድጋፍ እያረጉ እንደሚገኝ ታውቋል።ለኮሮና ቫይረስ እዳይጋለጡም በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።
በዘላቁነትም ችግሩን ለመቅረፍ በአካባቢው የሚከሰተውን ጎርፍ አደጋ መከላከል እንዲቻል በአዋሽ ተፋሰስ ልማት ፅህፈት ቤት የተሰሩ ጥናቶችን ወደ ተግባራ መቀየሩ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል እና በአፋር ክልሎች በቅርብ ሳምንታት በተከሰቱ ጎርፎች በርካቶች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው።