የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በአዲሱ በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 400 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
በዘርፉ ለ45 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታሰቡም ተገልጿል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ይህን ያለው በተያዘው በጀት ዓመት ለማከናወን በዕቅድ የያዛቸውን ሥራዎች አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ ነው፡፡
በኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግና ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ደርቤ ደበሌ እንዳሉት ኮርፖሬሽኑ በ2017 የዓለም ምርጥ የኢንዱስትሪ ፓርክ አልሚና አስተዳዳሪ የመሆን ራዕይ አንግቦ እየሰራ ነው።
ለዚህም ዘርፉን የሚመጥን ዕቅድ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው በበጀት ዓመቱ 36 የአገር ውስጥ አልሚ ባለሃብቶችን ወደ ፓርኮች ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
” በዚሁ ጊዜ ከ45 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከወጪ ንግድ 400 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ተይዟል” ብለዋል፡፡
የተገነቡ ፓርኮችን ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ በማስገባት የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ከማሳደግ ባለፈ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ይሰራልም ብለዋል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 165 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ወደ ውጭ መላኩን ለማወቅ ተችሏል።