የወርርሽኙን ስርጭትን መግታት ካልተቻለ በቱሪዝሙ ላይ የሚደርሰው ጫና እየባሰ እንደሚሄድ ቢሮው አስታወቀ።

245

የኮሮናቫይረስን ስርጭት ባጭሩ መግታት ካልተቻለ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኃይለየሱስ ፍላቴ ለአብመድ እንዳሉት በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ሩብ ዓመታት ዘርፉ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ነበር።
በበጀት ዓመቱ 12 ነጥብ 6 ሚሊዮን የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ለመሳብ ታቅዶ በሦስቱ ሩብ ዓመታት ብቻ (እስከ መጋቢት 30/2012 ዓ.ም) 11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ጎብኝዎች በክልሉ ተንቀሳቅሰው ጎብኝተዋል፡፡ ከዚህም 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ነው ያስታወቁት።

በዘጠኝ ወራቱ 25 ሺህ 435 የሥራ እድል መፈጠሩንም አቶ ኃይለየሱስ ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የተገኘው ገቢ፣ የሥራ እድል ፈጠራው እና የቱሪስት ፍሰቱ ካለፈው በጀትጨዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ማሳየቱንም አስታውቀዋል፡፡ ዓመታዊ አፈጻጸሙም ወደ እቅድ የተጠጋ እንዲሆን አድርጎታል።

በርግጥም በክልሉ ከፍተኛ የጎብኝዎች ቁጥር የሚኖረው በመጀመሪያዎቹ ሦስት ሩብ አመታት ነው። በእነዚህ ጊዜያት ከሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቦታዎች፣ ተፈጥሯዊ የጉብኝት መዳረሻዎች እና የባሕል ኢንዱስትሪዎች በተጨማሪ በርካታ ጎብኝዎች የሚታደሟቸው ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የአደባባይ በዓላት አሉ። ደብረታቦር (ቡሄ)፣ ሻደይ፣አሸንድዬና ሶለል ባዓላት፣ እንግጫ እና ከሴ ነቀላ፣ መስቀል እንዲሁም ደግሞ በተለይ በጎንደርና በምንጃር ሸንኮራ አረርቲ በስፋት የሚከበረውን የጥምቀት በዓላትን ጨምሮ በርካታ ሁነቶች ይበዛሉ።

የበጀት ዓመቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴና ገቢው የተሻለ የሆነው በዚህ ምክንያት መሆኑንም አቶ ኃይለየሱስ አመላክተዋል።

እንደ አቶ ኃይለየሱስ ማብራሪያ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየጨመረ መምጣቱ፣ ከአፍሪካ ሀገራ በሁሉም ዘርፍ ቀዳሚ ተጠቃሽ መሆኗ፣ ጥምቀትን ጨምሮ በክልሉ እና በኢትዮጵያ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶች ዓለምዓቀፍ እውቅና ማግኘታቸው፣ የክልሉ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱም ጭማሪ እንዲኖር ካደረጉት መካከል ተጠቃሾች ናቸው። ይህንን ተከትሎም የመስተንግዶ ተቋማት ደረጃ የማደግ፣ ዘመናዊ እና ባሕላዊ የምግብ አዘገጃጀት እና ሥነ ምግባርን የተላበሰ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሠጣጥ መዳበሩን አመላክተዋል፡፡

ነገር ግን የወረርሽኙ መከሰት እና በፍጥነት መስፋፋት በዘርፉ የታየውን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ከጅምሩ ጎድቶታል፡፡ ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ካደረጉ ጥቂት ሰዎች በስተቀር ከሚያዝያ/2012 ዓ.ም እስከ በጀት ዓመቱ ማብቂያ ድረስ ምንም የውጪ ሀገራት ጎብኝዎች ወደ ክልሉ አልገቡም፡፡ የሀገር ውስጥ እንቅስቃሴው መቋረጡንም በማሳያነት አንስተዋል።

በዚህ የዘርፉ ተዋንያን ክፉኛ መጎዳታቸውን ተናግረዋል። በተለይም የኮከብ ደረጃ የተሰጣቸው እና ኮከብ መጥን አገልግሎት ሰጪ ሆቴሎች ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባቸዋል፡፡
እንደማሳያ በባሕር ዳር ከተማ ከሚገኙ ሆቴሎች መካከል 13 የሚሆኑት የኮከብ ደረጃ፣ 20 የሚሆኑት ደግሞ ኮከብ መጥን ደረጃ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሆቴሎች ብቻ 2 ሺኅ 254 ሠተኞችን ቀጥረው አሰማርተዋል፡፡ ምንም እንኳን የጉዳት መጠናቸው የሚለያይ ቢሆንም ሁሉም ሆቴሎች በወረርሽኙ ምክንያት ተጎድተዋል፡፡ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ የነበራቸው ሆቴሎች 40 ሺኅ ፣ እስከ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ያገኙ የነበሩት ደግሞ 56 ሺህ ብር ብቻ ማግኘታቸውም በዳሰሳዊ ጥናት ተረጋግጧል፡፡ እንደ አቶ ኃይለየሱስ ገለጻ በክልሉ የኮከብ ደረጃ ያላቸው እና ኮከብ መጥን አገልግሎት የሚሰጡ ከ90 በላይ ሆቴሎች ቀጥተኛ የችግሩ ተጠቂዎች ሆነዋል፡፡

በሌላ በኩል በባሕል ኢንዱስትሪው የተሠማሩትም ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡ በደሴ፣ባሕር ዳር እና ጎንደር ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የተለያዩ የባሕል ኢንዲስትሪዎች ለ 4 ሺህ 54 ሰዎች ሥራ ፈጥረው ነበር፡፡ ዘርፉ በክልሉ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ቢፈጥርም በወረርሽኙ ሳቢያ ከሥራ ውጪ ሆነዋል፡፡

የወረርሽኙ ስርጭት ባለበት የሚቀጥል ከሆነም የችግሩ አሳሳቢነት እንደሚጨምር አብራርተዋል። ነሐሴ አጋማሽ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ባልተለመደ መልኩ ሕዝብ ተሰብስቦ እንዳያከብራቸው ተደርጓል። ምናልባት የችግሩ አሳሳቢነት እየታዬ ሌሎች በዓላትም በዚሁ በዚሁ መልኩ ሊከበሩ እንደሚችል አመላክረዋል። በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ውሳኔው የሚተገበር ከሆነ በ2013 የበጀት ዓመት ቱሪዝሙ በፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳ ጠቅሰዋል።

በዘርፉ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በተወሰነ መልኩ ለመቀነስ የክልሉ መንግሥት የቱሪዝም ማገገሚያ አሠራሮችን እየተገበረ እንደሆነ ተናግረዋል። በክልሉም ሆነ እንደ ሀገር ወረርሽኙ በቱሪዝሙ ላይ የሚያደርሰውን ጉልህ ተጽዕኖ ለማስቀረት መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር በዘርፉ የተሰማሩ አካላት አሠራራቸውን ቢቀይሩ የተሻለ እንደሚሆንም አመላክተዋል። ከምንም በላይ ግን የወረርሽኙን ሥርጭት መቋጨት እንደሚገባ ነው አቶ ኃይለየሱስ ያመለከቱት።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

Previous articleለመምረጥ ይቸገር የነበረው ሕዝብ ላለመምረጥም ተቸግሯል፡፡
Next article“ዶላሩ በመቅረቱ ከጉዳቱ ይልቅ ጠቀሜታው ያመዝንብኛል።” ዶክተር አረጋ ሹመቴ