ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 21/ 2012 (አብመድ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2012 በጀት ዓመት የእቅዱን 80 በመቶ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል።
ተቋሙ ያለፈውን በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2013 በጀት ዓመት የትኩረት መስኮች በተመለከተ ዛሬ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በ2012 በጀት ዓመት የሀይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ 405 ከተሞችና መንደሮች ላይ የፕሮጀክት ሥራወችን ለመከወን ታቅዶ 325 ከተሞችና መንደሮችን ማገናኘት እንደተቻለ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በተደረገው ጥረት ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ የደንበኞችን ቁጥር ከ168 ሺህ 700 በላይ ማሳደግ እንደተቻለ ነው አቶ ሺፈራው የገለጹት። ከሀይል ሸያጭ 11 ነጥብ 06 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ይህም የእቅዱን 80 በመቶ መሆኑን አስረድተዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመት ደግሞ 50 ሺህ የሚደርሱ አዳዲስ ዘመናዊ የመብራት ቆጣሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዷል።
ከዓለም ባንክ 400 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት እየሠራ እንደሆነም በመግለጫው ተመላክቷል። ይህም የተጀመሩ ሥራዎችን ለመደገፍ የሚውል እንደሆነ ነው የተገለጸው።
የሀይል መቆራረጥ፣ የመስመሮች ስርቆት፣ የሠራተኞች ስነ ምግባር፣ የጥገና ብቃትና ፍጥነት አለማደግ፣ የሀይል ብክነት፣ ተደራሽነት እና ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ፈጥኖ አለመፍታት አሁንም መፈታት ያለባቸው ችግሮች መሆናቸው በመግለጫው ተመላክቷል።
ለፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሬ የማግኘት ችግርም ለአፈጻጸም እንቅፋት መሆኑ ተመላክቷል። በመፍትሔነትም ከውጭ የሚገቡትን እቃዎች በሀገር ውስጥ የማምረት ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።
የቆጣሪ ንባብ አሠራሮችን የማሻሻል ሥራው በሦስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ጋሻው ፋንታሁን