ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 14/2012 (አብመድ) ከነሐሴ 1 እስከ 14/2012 ባሉት ሁለት ሳምንታት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የማድረግ ዘመቻው መሳካቱን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገልጿል፡፡
በ14 ቀናቱ ለ 50 ሺህ 50 ሰዎች ምርመራ ለማድረግ ታቅዶ 60 ሺህ 514 ሰዎችን መመርመር እንደተቻለ ነው ቢሮው ያስታወቀው። የቢሮው ኃላፊ መልካሙ አብቴ (ዶክተር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ መሠረት የምርመራ ክንውኑ ከእቅዱ አንጻር 120 ነጥብ 9 በመቶ ነው።
በዘመቻው በ 1 ሚሊዮን 963 ሺህ 151 ቤቶች በመዘዋወር ቅኝት ተደርጓል። በዚህም ለ 6 ሚሊዮን 347 ሺህ 812 ሰዎች ግንዛቤ ተፈጥሯል ብለዋል ዶክተር መልካሙ። ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየውም 7 ሺህ 351 ሰዎች የመተንፈሻ ችግር እንዳለባቸው በዘመቻው ተለይተዋል።
የሥራ ኃላፊዎች በቅንጅት መሥራታቸው፣ ማኅበረሰቡ የምርመራን ጥቅም አውቆ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ናሙና መስጠቱ፣ የበጎ ፈቃደኞች ርብርብ ከፍተኛ መሆን፣ የብዙኃን መገናኛዎች ሰፊ ሽፋን መስጠታቸው እንዲሁም ከጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥሩ ድጋፍ መኖሩ ስኬታማ አፈጻጸም እንዲኖር ሚና እንደነበራቸው በመግለጫው ተመላክቷል።
የምርመራ ዘመቻው በቀጣይ ጊዜያትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቁት ቢሮ ኃላፊው ኅብረተሰቡ ከህክምና ባለሙያዎች የሚተላለፉ የመከላከያ ዘዴዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡
በደጀኔ በቀለ