‘ከውጫሌ ውል እስከ አድዋ ድል የኢትዮጵን ታሪክ ይዘክራል’ የተባለው የባሕል ማዕከል ግንባታ ተጠናቀቀ።

442

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 14/2012 (አብመድ) ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ከጣልያን ጋር የውጫሌ ስምምነትን በተፈራረሙበት ታሪካዊ ቦታ ላይ የተገነባው የይስማ ንጉሥ የባሕል ማዕከል ግንባታ መጠናቀቁን የአምባሰል ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ጽሕፈት ቤቱ እንዳስታወቀው ግንባታው የመግቢያ በር፣ ሙዚዬም እና ካፌን ያካትታል። በአጠቃላይ 25 ሚሊዮን 734ሺ 720 ብር ወጪ እንደተደረገበትም ጽህፈት ቤቱ አስታወቋል።

የባሕል ማዕከሉ የተገነባው የአካባቢውን ባሕል ለማስተዋወቅ፣ ሀገራዊ ፍቅር እና አንድነትን ለማስተማር፣ ታሪክን ለማስረዳት እና ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ለማቆየት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ታስቦ ነው። ከውጫሌ ውል እስከ አድዋ ድል የኢትዮጵያ ታሪክን ሊገልጽ በሚችል መልኩ ታስቦ እንደተሠራም ተጠቅሷል። በተለይም የጥቁሮችን የአሸናፊነት መንፈስ የሚያንጸባርቁ ይዘቶች እንዳሉትም ተመላክቷል።

በእነዚህ ጊዜያት የነበሩና የኢትዮጵያ ታሪክን የሚገልጹ ታሪካዊ ቅርሶችን ከፌዴራሉ እና ከክልሉ መንግሥታት እንዲሁም በስጦታ፣ በውሰት፣ በግዥ እና በውርስ መልኩ በማኅበረሰቡ እጅ የሚገኙ ልዩልዩ ቅርሶችን ሰብስቦ ወደ ሙዚየሙ ለማስገባት እንቅስቃሴ እንደተጀመረም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

የጽሕፈት ቤቱ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ባለሙያ ወይዘሪት የውብዳር ሺበሺ ለአብመድ በስልክ እንዳሉት ማዕከሉን ለጎብኝዎች ክፍት ለማድረግ የአደረጃጀት ሥራ እየተሠራ ነው፤ ነገር ግን በምን ያህል ጊዜ አደረጃጀቱ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ እርግጠኛ አይደሉም። ቅርሶቹ ወደ ሙዚዬሙ ገብተውበት ለጉብኝት ክፍት ሲሆንም የአካባቢው ማኅበረሰብ የቱሪዝም ኢኮኖሚው ተጠቃሚ ይሆናል።

ታህሳስ 4/2010 ዓ.ም የግንባታ ውል የተያዘለትን የባሕል ማዕከል በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ሂደቱ በመጓተቱ የካቲት ላይ መጠናቀቅ የነበረበት የርብክብ ስነ ሥርዓት ዘግይቷል።

በሰኔ መጨረሻ መጀመሪያ ዙር የርክክብ ስነ ሥርዓት ሲከናወንም መስተካከል የነበረባቸው የማጠቃለያ ሥራዎች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ተሰጥቶ ነበር። ማስተካከያው ተሠርቶ የፊታችን ነሐሴ 17/2012 ዓ.ም የክልል የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የርክክብ ሥነሥርዓቱ ይከናወናል።

ይስማ ንጉስን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የክልሉ መንግሥትም ሆነ ዞኑ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆኑን ባለሙያዋ አስታውቀዋል አስታውቀዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብም የእርሻ ማሳቸውን ለግንባታው ከመልቀቅ ጀምሮ ማዕከሉ እንዲገነባ እስከ ክልል ድረስ ሄደው በጀት በማስመደብ ትልቅ ሚና ነበራቸው። አብመድም የግንባታውን አፈጻጸም እየተከታተለ በተደጋጋሚ ዘግቧል።

ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ

Previous articleበማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ በተደረገው የምርመራ ዘመቻ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ80 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
Next article‘ከውጫሌ ውል እስከ አድዋ ድል የኢትዮጵን ታሪክ ይዘክራል’ የተባለው የባሕል ማዕከል ግንባታ ተጠናቀቀ።