ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/2012 (አብመድ) በማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ በተደረገው የኮሮና ቫይረስ የምርመራ ዘመቻ ቀድሞ ከነበረው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ80 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሁለት ሳምንታት ለመመርመር ከታቀደው 200 ሺህ ሰው ባለፉት 12 ቀናት ከ182 ሺህ በላይ ሰዎችን መመርመር መቻሉ ታውቋል።
በኢትዮጵያ ኮሮና ከመከሰቱ በፊትና ከተከሰተ በኋላ ማኅበረሰቡ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳይጎዳ በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል ብሏል ሚኒስቴሩ።
ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ውጤቶች ቢገኙም በተግባር የመከላከል ስራው ላይ ክፍተት ስላለ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱንም አስታውቋል።
ይህንን ሁኔታ ለመቀየርና በሽታውን በጽናት ለመከላከል አንድ ወር የሚቆይ የማኅበረሰብ አቀፍ የንቅናቄና የግንዛቤ ዘመቻ ”ምክንያት አልሆንም” በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ባለፉት 12 ቀናት በዘመቻው የተከናወኑ ስራዎችን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የማኅበረሰብ አቀፍ የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ከተጀመረበት ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል። በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች የሚገኙት በማኅበረሰብ ውስጥ በሚደረግ አሰሳ መሆኑንም ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።
እየተገኙ ያሉ ውጤቶችም ለቀጣይ ውሳኔዎችና መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች መረጃ እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ባለፉት 12 ቀናት 182 ሺህ 497 ሰዎችን በመመረመር በሁለት ሳምንታት ብቻ ከታቀደው 200 ሺህ ሰዎች የዕቅዱን 92 በመቶ ማሳካት መቻሉን ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በአማካይ በየቀኑ 15 ሺህ ሰዎችን በመመርመር ቀድሞ ከነበረው የምርመራ አቅም 78 በመቶ ማሳደግ ተችሏልም ነው ያሉት ሚኒስትሯ።