ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/2012 ዓ.ም (አብመድ)በዓለ ደብረታቦር በደብረታቦር ከተማ በደማቅ ሀይማኖታዊና ባሕላዊ ስነስርዓት ተከብሯል፡፡ በደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን በተከበረው የበዓለ ደብረታቦር ስነስርዓት ላይ የተገኙት የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በዓለ ደብረታቦር ኢየሱስ ወልደ ማርያምና ወልደ አብ መሆኑን የገለጠበት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል፡፡
ብፁነታቸው የኢትዮጵያዊው ደብረታቦር ተራራ ኢየሱስ ከተገለጠበት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለውም አንስተዋል፡፡ የእኛ ታሪክ እስረኤል ሀገር በሚገኜው የታቦር ተራራ ላይ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው በዚያ ተራራ ላይ ታላቅ የኤሊያስ ቤተክርስቲያን አለ በውስጥ ተስሎ የሚገኝ ‹‹ኢትዮጵያ እጀቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚል ጽሁፍ ጋር ጠይም ሴት ተስላ እንደምትገኝም አስታውሰዋል ፡፡
ኢትዮጵያ የተገለጠችው በዚያ ተራራ ላይ ነውም ብለዋል፡፡ ከተራራው ወረድ ብሎ ጥብርያዶስ ከሚባል ባሕር ላይም ሶስት የንግሥት ሳባ መርከቦች ተስለው እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡ በግልጽም ይታያሉ ብለዋል፡፡
ታሪኩም ከዛኛው ኢትዮጵያ ብርሃነ መለኮቱ ከተገለጠበት ተራራ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቦታን ሲያከብሩት ያከብራል፣ ታሪክን ሲያከብሩት ያከብራል ታሪክን ከጨመሩበት እርግማን ነው፡፡ ከቀነሱበት ደግሞ ጥፋት ነው፡፡ ታሪክ በታሪክነቱ ቀጥታ ሲኖር የሚቀጥለው ትልውድ አክብሮ ይይዘዋል፡፡ በታሪክም እንባረካለን፡፡›› ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መልካም ታሪክ የሰራ ስሙ ሕያው ይሆናል ያሉት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ልጆች እንዳባቶቻቸው እንዲሆኑም አደራ ብለዋል፡፡
የወቅቱ ስጋት የሆነው ኮሮና ቫይረስ ጥንቀቄ እንዲያሻ ያመላከቱት ብፁእ አቡነ ሚካኤል ሰው ከሌለ ምንም እንደማይኖርም ተናግረዋል፡፡
አልምኮቱና ምስጋናው የመጻሕፍቱ ሚስጥር የሚገለጠውም ሰው ልጅ ሲኖር ብቻ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡ ራሳችን በራሳችን መጠንቀቅ አለብን እግዚአብሔርን እናምናለን እንዳመነውም ይደረግልናል እኛ የሚጠበቅብንን ግን ማድረግ ይገባናል ነው ያሉት፡፡
በታርቆ ክንዴ