በዓለ ቡሄ እና ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር

1006

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/1012 ዓ.ም (አብመድ)ከተማዋ የከተመችው የሃገር ጣራ በሆነ ከፍተኛ ቦታ ላይ ነው፤ በዚያ ላይ ተራራ ተጨምሮበት የከፍታውን መጠን በእዝነ ህሊና መሳል ለማንም አይከብድም፡፡

የዳግማዊ ቴዎድሮስ የጥበብ እጂ የተፈታበት፤ የራስ ጉግሳ ወሌ የጦር መነፀር ነው፤ ማማው ደብረ ታቦር፡፡ በሃገረ እስራኤል የሚገኘው የደብረ ታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮት የተገለጠበት ተራራ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ኢትዮጵያዊው ደብረ ታቦር ደግሞ የጨለማው ወቅት መጋመስ የብርሃን ወቅት መምጣት ተብሲር የሚገለፀበት ተራራ ነው፡፡
‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኽ የለም ሌሊት›› የሚባለውም ለዚያ ነው፡፡ ከታቦር ተራራ ላይ የሚወጣው የእረኞች የጂራፍ ጩኽት እና ሆያ ሆየ የሚል አዝማች የሚበዛበት የህፃናት ህብረ ዝማሬ የአዲስ ዘመን መምጣት ብስራት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡

ከታቦር ተራራ መሳ ለመሳ አሻግሮ የሚስተዋለው የጉና ተራራ፣ ወዲያ ማዶ የተዘረጋው የጣና ሐይቅ፣ ከአድማስ በታች የሚስተዋለው የደንቢያ ምድር እና የተከዜ ተፋሰስ እርካብ የሆነው የበለሳ ምድር ተቀባብለው ያደምቁት ይመስል የህብረ ዝማሬው ድምፅ በዚህ ወቅት ጎልቶ ይሰማል፡፡

‹‹ደብረ ታቦር›› በክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ብርሃኑን በደብረ ታቦር ተራራ እንደተገለጠ በማሰብ ‹‹የመገለጥ›› በዓል ተደርጎ ይከበራል፡፡ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ደግሞ ከሐይማኖታዊ ክብረ በዓል ባለፈ ማህበራዊ አንድምታም አለው፡፡ በወቅቶች መፈራረቅ ዝናብ የበዛበት የጭፍና ወቅት አልፎ አዲስ ዘመን አዲስ ብርሃን ይዞ የመምጣት ተስፋን ለመግለፅ ‹‹የብርሃን›› ወይም ‹‹ቡሄ›› በዓል እየተባለ ይከበራል፡፡

በታቦር ተራራ በየዓመቱ ወርሃ ነሐሴ ላይ የሚከበረው የቡሄ በዓል ልዩ ልዩ ሐይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ማህበራዊ መስተጋብሮች ይከወናሉ፡፡ የተወሰኑትን እንመልከት፡፡ ከቡሄ በዓል ጋር ተያይዞ የማይረሳ ድባብ ያለው ታቦር ተራራ ላይ የሚሰማው የእረኞች የጅራፍ ድምፅ ነው፡፡
በሐይማኖታዊ አስተምህሮው የኢየሱስ ክርስቶስን ግርፋት ለማመስጠር ነው፡፡ የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የጅራፉ ድምፅ እረኞች አዝርዕትን ከአዕዋፍት ለመጠበቅ ጊዜው መቅረቡንም ማመልከቻ ነው ይላሉ፡፡ ሌላው በቡሄ በዓል ከሚስተዋሉት ትዕይንቶች መካከል አንዱ ደግሞ ችቦ ነው፡፡ ችቦው በሐይማኖታዊ አስተምህሮ የራሱ ትርጉም ቢኖረውም የጨለማ መገፈፍ እና የብርሃን ምሳሌ ሆኖ ያገለግላል፡፡

የቡሄ ዳቦ ወይም ሙልሙል በዚህ ወቅት እረኞች በጋራ የሚመገቡት ምግብ ነው፡፡ እረኞች በህብረ ዝማሬ ታጅበው እና ችቦ ለኩሰው ‹‹ሆያ ሆየ›› እያሉ በሄዱበት ሰፈር ሁሉ እናቶች ሙልሙል ጋግረው ይሰጧቸዋል፡፡ በችቦው ብርሃን የልጆቻቸውን መምጣት ወጥተው የሚፈልጉት እናቶች የጋገሩትን የቡሄ ዳቦ እየሰጡ ከዓመቱ ያድርሳችሁ፤ ያሳድጋችሁ እያሉ ይመርቋቸዋል፡፡

ዳቦውን የሚሰጡት እናቶች ምርቃን የልጆቹን ጭፈራ የብርሃን ጊዜ መምጣት መልዕክተኛ፣ የጥልቅ ቤተሰባዊነት መተሳሰር እና የአዲስ ዘመን ንጋት አብሳሪ አድርገው ስለሚወስዷቸው ነው፡፡ ‹‹ሆያ ሆየ ጉዴ፤ ሙልሙል ይላል ሆዴ!›› እያሉ እና እየጨፈሩ ሰፈሩን ሁሉ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ብስራት ያደምቁታል፡፡ ዘንድሮ ደብረ ታቦርን እና በዓለ ቡሄን በደብረ ታቦር ይከበራል፤ እኛም መልካም የቡሄ እና የደብረ ታቦር በዓል እንዲሆን ተመኘን፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleበጎንደር ዙሪያ ወረዳ ከሰሞኑ በደረሰ የመሬት መንሸረታት አምስት የቤተሰብ አባላት ሕይወት አለፈ፡፡
Next article‹‹ቦታን ሲያከብሩት ያከብራል፣ ታሪክን ሲያከብሩት ያከብራል ታሪክን ከጨመሩበት እርግማን ነው፡፡ ከቀነሱበት ደግሞ ጥፋት ›› ብፁዕ አቡነ ሚካኤል