ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/1012 ዓ.ም (አብመድ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ደብረሰላም ቀበሌ ከሰሞኑ በጣለው ከባድ ዝናብ በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት አምስት የቤተሰብ አባላት ሕይወታቸው አልፏል፤ ሀብትና ንብረታቸውም በናዳው ጠፍቷል፡፡
የተጎጂዎች ቤተሰብ ቄስ ዓለሙ ሞትባይኖር ለአብመድ እንደተናገሩት እህታቸው ከባለቤታቸውና ከሶስት ልጆቻቸው ጋር ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ናዳው በሌሊት በመከሰቱ ተጎጂዎች ሰው ሳይደርስላቸው እንደቀረ የተናገሩት ቄስ ዓለሙ እስከቤቱ ተደርምሶ እንደተገኙ ተናግረዋል፡፡ ሕይወታቸውን ያጡት ቤተሰቦች ሁለት ልጆቻቸው በወቅቱ ከቤት ስላልነበሩ ተርፈዋል ነው ያሉት፡፡ ልጆቹ አሁን ላይ ረዳት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡ በመንግሥት በኩልም እስካሁን ድረስ መጥቶ ከማዬት የዘለለ ነገር የተደረገ ድጋፍ አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡
ናዳው አምስት የቤተሰብ አባላቱን ከማጥፋቱም በላይ በአካባቢው ማኅበረሰብ ሰብል ላይ ገዱት ማድረሱንም ተናግረዋል፡፡ አካባቢው ከአሁን ቀደም እንደዚህ አይነት አደጋ ተከስቶበት እንደማያውቅ ያስታወሱት ቄስ ዓለሙ እንደከዚህ ቀደሙ ምንም አይፈጠር በማለት እንደተዘናጉ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው የተናገሩት፡፡ አሁንም በተራራው ግርጌ የሚኖሩ የማሕበረሰብ ክፍሎች በስጋት ላይ እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡ ለማሕበረሰቡም ጊዜያዊ መጠለያ መዘጋጀት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡ ዝናብ በዘነበ ቁጥር መደናገጥ እየተፈጠረ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤትም በስምንት ሔክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።
በዚሁ ወረዳ ሰንደባ ቀበሌ በረዶ ቀላቅሎ በጣለው ዝናብ በሰብላቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን የቀበሌው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በጣለው ከባድ ዝናብ ቀደም ብለው በ137 ነጥብ 45 ሔክታር መሬት ላይ በተዘሩ ሰብሎች ላይ ጉዳት ማድረሱንም የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ ከሰብሉ መጎዳት በተጨማሪ የመሬት መንሸራተት እና ባልተለመደ በመልኩ መሬቱ መሰነጣጠቅ ስጋት እንደሆነባቸው ነው ብለዋል፡፡
የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ ውበት መስፍን በሁለቱም ቀበሌዎች ላይ የአደጋውን መጠን የሚገመግም ቡድን ወደ ስፍራው ልከው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በደረሰው ግምገማ መሰረትም የምግብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መጨረሳቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ቀሪ ቤተሰቦች የዘመዶቻቸውን ሕይወት ብቻ ሳይሆን ቁሳቁስም ስለወደማባቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የመደርመስ አደጋ በደረሰበት አካበቢ በስጋት እየኖሩ የሚገኙ የማሕበረሰብ ክፍሎችን በአጭር ጊዜ ዕቅድ ከዘመደ አዝማድ እንዲጠጉና ከአካባቢው እንዲርቁ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡ ይህን ለማድረግ የግንዛቤ ፈጠራ የሚሰራ ባለሙያ መላካቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግን አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት ሥራ በመጠበቅና ከንክኪ በመራቅ ማደስ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡ በተራራው ግርጌ ኑሯቸውን የመሠረቱ ማሕበረሰቦችን በአንድ አካባቢ የማስፈር ሥራ መስራት እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ውበት ይህን ለማደረግ ከማህበረሰቡ ጋር ምክክር ማድረግ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የዝናብ መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ በወረዳው ሌሎች ቀበሌዎች ላይም ተመሳሳይ ችግር ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል ያሉት አስተዳደሪው በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የጥንቃቄ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡ በየቀበሌዎች የሚታዬውን የመሬት መሰነጣጠቅ በዘላቂነት ለመፍታት በዘርፉ ባለሙያዎች ጥናት ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡ በሰንደባ ቀበሌ ላይ በደረሰው የሰብል ጉዳት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰብሎች በቶሎ በሚደርሱ ሰብሎች የመቀዬር ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
ወረዳው በሚችለው ሁሉ ድጋፍ እያደረገ ከአቅሙ በላይ የሆነውን ደግሞ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ እንደሚቀርብም ተናግረዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ክረምቱን በሰላም ለማለፍ ጥንቃቄ ማደረግ እንደሚገባው ያሳሰቡት ዋና አስተዳደሪው ችግር ሲፈጠርም ርዕስ በርእስ የመዳጋገፍ ባሕሉን እንዲያጎለብት ጠይቀዋል፡፡
በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በሁለቱም ቀበሌዎች በ145 ነጥብ 45 ሔክታር መሬት ላይ በተዘሩ ሰብሎች ላይ ጉዳት መድረሱንና በዚህም 323 አባወራ እና እማወራዎች ለጉዳት መዳረጋቸው ተገልጿል። በሰንደባ ቀበሌ ደግሞ የመሬት መሰንጠቁ አሁንም ስጋት መደቀኑ ታውቋል።
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ