ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከ2011 በጀት ዓመት የ35 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሀገር ውስጥ ታክስ፣ የውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ የገቢ ዕድገቱ ከ2011 በጀት ዓመት አንጻር እድገት ማስመዝገቡን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ለገቢ አፈጻጸሙ ውጤታማነት የአሰራር ስርዓት መሻሻል፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ ለሕግ ተገዥነትን ማሻሻል ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸውም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን የገቢ አፈጻጸሙ በዚህ በጀት ዓመት ጭማሪ ቢያሳይም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው አንጻር ሲታይ ግን አመርቂ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከቀጥታ እና ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች የምታገኘው ገቢ ከሀገራዊ ምርት አንጻር ሲታይ ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት አማካይ ያነሰ በመሆኑ ወደ ፊት ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ያለው የታክስ አስተዳደር ተገልጋዩን አርኪ እና ለህግ ተገዢነትን ያረጋገጥ እንዲሆን ለማስቻል በርካታ የሪፎርም ሥራዎች በመሠራት ላይ መሆናቸውን አቶ ላቀ አስታውቀዋል። ከእነዚህም መካከል የጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥን የተቀላጠፈ እና “ዲጂታል” ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ 2013 በጀት ዓመት የገቢ ዕቅዱም 290 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱ ታውቃል፡፡ከእዚህ ውስጥ በሐምሌ ብቻ 19 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታዕቅዶ 21 ነጥብ 5 ቢሊዮን ወይም የዕቅዱን 110 ነጥብ 64 በመቶ ተፈፅሟል ብለዋል::
ከ2012 የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር አንፃርም የ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ዕድገት አለው ብለዋል ሚኒስትሩ።
ዘጋቢ፦ ጋሻው ፈንታሁን-ከአዲስ አበባ