ቡሄ የመስጠትን እና የልግስናን እሴት ያስተዋውቃል፡፡

423

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/2012 ዓ.ም (አብመድ) የቡሄ ታሪካዊ ዳራ እና መልካም እሴቱ!

እንደ ስብጥሯ የደመቀ እንደ ቋንቋዋ የረቀቀ ታሪክ ባለቤት ሀገር-ኢትዮጵያ፡፡ ዓመት እየጠበቀች የምታከብራቸው እልፍ በዓላት አሏት፡፡ ወቅት እየተጠበቁ የሚከበሩ በዓላትም ዘፈቀዳዊ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከአስተሳሰብ፣ ከእሴት፣ ከእምነት፣ ከጀግንነት እና ከማንነት ጋር የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የምታከብራቸው በዓላት የማንነት አሻራ ውርስም ጭምር ናቸው፡፡

ከእነዚህ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድርም አሸዋ ከበዙ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ትውፊት ካላቸው በዓላት ውስጥ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበረው የቡሄ በዓል አንዱ ነው፡፡ እኛም ስለ ቡሄ ወይም የደብረ ታቦር በዓል ታሪካዊ ዳራ እና አሁን ያለበትን ሁኔታ ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡ የቡሄ ወይም የደብረ ታቦር በዓል ባህላዊም ሃይማኖታዊም ህብረ ቀለም አለው፡፡ ‘ቡሄ’ ማለት ቡሆ፣ መላጣ ወይም ደግሞ ገላጣ ማለት ነው፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢዎች ‘ቡሄ መጣ ሆ! ያ መላጣ ሆ!’ እየተባለ ይቀነቀናል፡፡

የዚህን ትርጓሜ አበው ሲተረጉሙት ጨለማን የለበሰው በዝናብ፣ በጎርፍ እና በጭጋግ የደበዘዘው ያ! የክረምት ወር አለፈ፡፡ በምትኩም ክረምቱን እንደ ምንም አልፈን ገላጣ፣ ብርሃን ከሚፈነድቅበት እና የአዲስ ሕይወት ብስራት ተሰፋ ከሚደረግበት መስከረም ላይ ደረስን ማለት ነው ይላሉ፡፡ አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ እና አዲስ ብስራት ይዞ ብቅ አለ ማለት እንደሆነ ባህላዊ ትውፊቱ ያመላክታል፡፡

ይህ ባህላዊ መሠረት ያለው በዓል በሌላ በኩል ሃይማኖታዊ ዘውግም አለው፡፡ ‘ደብረ ታቦር’ ወይም ‘የደብረ ታቦር በዓል’ በመባል ይታወቃል፡፡ ሃይማኖታዊ አስተምህሮውም እየሱስ ክርስቶስ በማስተማር ላይ በነበረበት ጊዜ በታቦር ተራራ ላይ “ብርሃነ መለኮቱ” ክብረ መንግስቱ የተገለፀበትን ጊዜ በማስታወስ የሚከበር ነው፡፡ በነሐሴ አጋማሽ ዋዜማ ሰሞን የበዓሉ ውብ ገፅታ እውን ይሆናል፡፡ ከማዶ እስከ ማዶ የሚያስተጋባ የጎረምሶች የጅራፍ ድምጽ የበዓሉን መምጣት ያበስራል፡፡ ውብ የሆኑ ህብረ ዜማዎች ከአንዱ ኮረብታ ወደ ሌላው ኮረብታ በፍቅር ይስተጋባሉ፡፡ ይህንን የሚሰሙ እናቶች ለልጆቻቸው ሙልሙል ዳቦ የሚሆን ቡሆ (ሊጥ) ያዘጋጃሉ፡፡ ቡሄ የመስጠትን እና የልግስናን እሴት ያስተዋውቃል፡፡

ከ10 ያላነሱ ወጣቶች በቡድን በቡድን ሆነው ‘በአውራጃቸው’ አማካኝነት ዜማ ያንቆረቁራሉ፡፡ ግጥሞቹ ምጡቅ እና ውብ ባህላዊ እሴቶችን የሚያጎሉ፣ዜማዎቹ ለሰሚ ሃሴትን የሚያደርጉ እና ወደ ራስ ማንነት የሚመልሱ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ቡድን የየራሱ አውራጅ ይኖረዋል፡፡ አልፎ አልፎም የአውራጅነቱን ሥራ በመተጋገዝ ይሠሩታል፡፡

‘አውራጅ’ ማለት ቡድኑን የሚመራ ዋና ዘፋኝ ማለት ነው፡፡ ግጥሞቹን አካባቢያዊ ለዛ እና ቃና አልብሶ አውራጅ ያስረቀርቃል፤ የቡድኑ አባላት በመቀበል ያስተጋቡታል፡፡
አንዳንድ አካባቢዎች በቡድን በቡድን ሆነው ችቦ ያቀጣጥላሉ፡፡ ነድዶ ያለቀውን ረመጥ የቡድን አባላቱ በአውራጃቸው መሪነት ሦስት ሦስት ጊዜ ይዘላሉ፡፡ በዚህ ሂደትም ለፈጣሪያቸው ምስጋና ይቀርባሉ፡፡ ‘ጨለማውን አሻግረህ ከብርሃን ስላደረሰከን እናመሰግንሃለን፡፡ አዲሱን ዓመት የሰላም፣ የደስታ፣ የፍቅር እና የጤና አድርግልን!’ የሚል መልካም ምኞት ይቀርባሉ፡፡

ትውፊቱ በሀገራችን ገጠራማ አካባቢዎች አሁንም ድረስ እስከ ማራኪ ወዘናው ድረስ አለ፡፡ ሃይማኖታዊ ትውፊቱም ሆነ ባህላዊ እሴቱ አሁንም አልደበዘዘም፤ ነገር ግን ይህ ውብ ባህል በከተሞች አካባቢ አልፎ አልፎ መልኩ ተቀይሮ ከነጭራሹ ቡሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንኳን የተረሳበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ የቡሄ ባህላዊ ውርስ በቀጣይ ትውልድ ጭራሹን ባዕድ እንዳይሆን ትኩረት ይሻል።

አብሮነትን፣ መተሳሰብን፣ መስጠትን፣ ፍቅርን፣ መልካም ምኞትን የሚገልፁ እንቁ ባህሎቻችንን ሳናውቅ በመዘንጋት፣ እያወቅንም በንቀት እያለፍናቸው ትውልዱን የምዕራባዊያን ባህል ናፋቂ እናደርገዋለን፡፡ ቱባ ባህሎቻችንን ለትውልድ በማውረስ ወጣቱን ወደ ተፈጥሮው እና ወደ ማንነቱ ለመመለስ እንደ ቡሄ አይነት በዓላት አስታዋሽ ሽማግሌ፣ መከታ ምስለኔ ይቁምላቸው፡፡

መልካም የቡሄ በዓል!

በታዘብ አራጋው

Previous articleየተከዜ የብረት ድልድይ በጎርፍ በመወሰዱ የነዋሪዎች እንቅስቃሴ መገደቡን የስሃላ ሰየምት ወረዳ አስታወቀ።
Next articleየገቢዎች ሚኒስቴር በ2012 በጀት ዓመት 233 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡