ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 11/2012 (አብመድ) የክልሉ ትራንስፖርት ቢሮ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔዎች መጠናታቸውን አስታውቋል።
ችግሩ በየዓመቱ ለሦስት እና ለአራት ወራት የሚዘልቅ ቢሆንም አሁን ግን ከፊሉ የብረት ድልድይ በጎርፍ በመወሰዱ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ወረዳው ጠይቋል።
ከሰቆጣ- ዝቋላ – ስሀላ ሰየምት በሚያደርሰው መንገድ ላይ የተከዜ ሰው ሰራሽ የኃይል ማመንጫ ውሀ ያረፈበት ቦታ ይገኛል። ሰው ሠራሽ ኃይቁን አቋርጦ የተሠራው የብረት ድልድይ በውሀ በመሞላቱ ግን ትራንስፖርት ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ ሳምንት ሆኖታል።
የስሀላ ሰየምት ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻው ቸኮለ የብረት ድልድዩ በውሀ መዋጥ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ክፍሎች በጎርፍ መወሰዳቸውን ለአብመድ ተናግረዋል።
በጊዜያዊነት ትራንስፖርት በመቋረጡና የፈረሰውን ድልድይ በዘላቂነት ለመሥራት በርካታ ወራት የሚጠይቅ በመሆኑ ከ39 ሺኅ በላይ በሚሆኑ የወረዳው ነዋሪዎች ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎችም መስተጋብራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል ብለዋል።
በየክረምቱ በተከዜ የሰው ሠራሽ ሀይቅ አማካኝነት ችግር የሚገጥመው የብረት ድልድይ በዘላቂነት እንዲፈታ የወረዳው አስተዳደርና ሕዝቡ በተደጋጋሚ ለክልሉ ቢያሳውቁም ምላሽ ባለመሰጠቱ ዘንድሮም መቸገራቸውን አቶ ጋሻው ተናግረዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ ሰለሞን እሸቱ በተከዜ የኃይል ማመንጫ ውሃ ምክንያት ለሰመጠው የብረት ድልድይ ተለዋጭ የኮንክሪት ድልድይ እንዲሠራ አስተዳደሩ በየዓመቱ ለክልልና ለፌዴራል መንግሥታት ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርብም ምላሽ ባለማግኘቱ አሁንም ለችግር መጋለጣቸውን አመልክተዋል።
የፈረሰው ድልድይ ሥራ በአጭር ጊዜ እንዲጀምር ማድረግ ባለመቻሉ ችግሩን ለመቀነስ ካለፉት ከቅዳሜና እሁድ ጀምሮ ትራንስፖርቱን በየብስ እና በጀልባ በመቀባበል ማስቀጠላቸው ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ የኮንትራት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ምሕረት እውነቱ የስሃላ ሰየምት የብረት ድልድይ ላጋጠመው አደጋ ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት በባለሙያዎችና በአማካሪዎች ጥናት ተደርጎ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የጥገና ባለሙያዎች እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠይቋል ብለዋል።
ለድልድዩ ዘላቂ መፍትሔ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከአምባ ጊዮርጊስ-ዐብይ አዲ መገንጠያ የሚል የአስፓልት መንገድ እቅድ ውስጥ ተካትቶ መጠናቱንም ገልጸዋል።
የዘርፍ ኃላፊው በክልሉ ክረምትን መሠረት በማድረግ የተጎዱ ድልድዮችን አስቸኳይ ለመጠገን ጥናት ተሠርቶ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የተከዜ ድልድይ በጎርፍ በመወሰዱ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔዎች ተጠንተዋል ቢባልም ጥናቶቹ መቼ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ክልሉ ያስቀመጠው መረጃ የለውም።
ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ