
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 11/2012 (አብመድ) በአንድ ወር ብቻ ክልሉን ከ639 ሺህ ብር በላይ ያሳጣ ህገ ወጥ የአሳ ንግድ መካሄዱን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል።
በቢሮው የእንስሳት እና እንስሳት ተዋጽኦ ግብይት ዳይሬክተር አንተነህ ዓለሙ በ2012 በጀት ዓመት በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ሲካሄድ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በኮሮና ወረርሽን ምክንያ ከማቆሙ በፊት
15 ሺህ 900 ኪሎ ግራም አሳ ወደ ውጭ መላኩን ለአብመድ ገልጸዋል። ከዚህም ከ797 ሺህ ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል።
ይሁን እንጂ የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በመቆሙ የህገ ወጥ ንግድ መበራከቱን አቶ አንተነህ አንስተዋል። በ2012 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ለተላከው ምርት ማነስም የህገ ወጥ ንግድ መበራከት አንዱ ምክንያት መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ችግሩን ለመከላከል ቢሮው ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በጋራ የመቆጣጠር ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ነግረውናል። በዚህም መሠረት ባለፈው ሐምሌ 11 ሺህ 28 ኪሎ ግራም አሳ በመተማ በኩል በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሲወጣ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አቶ አንተነህ ገልጸዋል። ከዚህም ከ639 ሺህ ብር በላይ ገቢ መታጣቱን ዳይሬክተሩ ነግረውናል።
ምርቱ ለሀገር ውስጥ ገበያ ቀርቦ ቢሆን ደግሞ 3 መቶ 80 ሺህ ብር ገቢ ማግኘት ይቻል እንደነበር አቶ አንተነህ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ