
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 10/2012 (አብመድ) በኢትዮጵያ ዘርን፣ ሀይማኖትንና ማንነት ላይ ያተኮሩ የሚመስሉ ግጭቶች ዳግም እንዳይከሰቱ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለማምጣት ከመንግሥት ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።
ጉባኤው በቅርቡ በሻሸመኔና አካባቢው በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች በተከሰቱ ረብሻዎች በጠፋው የሰው ሕይወትና በወደመው ንብረት ምክንያት የተፈጠረውን አለመረጋጋት ወደ ቀድሞ ሠላሙ እንዲመለሥ እየሠራ መሆኑን ገልጿል። በኅብረተሰብ መካከል እርቀ ሠላም እንዲሰፍን ለማድረግም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በአንዳንድ ቦታዎች ዘርን፣ሃይማኖትንና ማንነትን መሠረት ያደረጉ የሚመሥሉና የሰው ሕይወት የሚቀጥፉ፤ ንብረት የሚያወድሙ ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው።
በቅርቡም በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ረብሻ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ አንዱ ማሳያ ነው።
ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ናቸው፤ የሃይማኖት ተቋማቱ ጉባኤ በሀገሪቱ ተጠብቆ የቆየው የመተባበርና የመከባበር እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሠራ ነው ብለዋል።
በተለይም በቅርቡ በሻሸመኔና አካባቢው ተከስቶ በነበረው የሰው ሕይወትና ንብረት ያወደመው ረብሻ በንጹሃን የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የጣለውን መጥፎ ጠባሳ በማክሰም፤ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን ጠቅላይ ጽሐፊው ለኢዜአ ተናግረዋል።
በጥቃቶቹ ላይ የየእምነት ተቋማቱ ተከታዮች ተሳትፈዋል ብሎ ጉባኤው እንደማያምን የጠቆሙት ሊቀ ትጉሃን ታጋይ፤ ከ98 በመቶ በላይ የሚሆነው የእምነቱ ተከታይ ጉዳቱ እንዳይስፋፋ ሲከላከልና የጥቃቱ ሰለባ ሲሆን እንደነበረም በቦታው በመገኘት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
እንዲህ ዓይነቶቹ መሰል ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ መንግሥት የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ማሳሰቡን ጠቅላይ ጽሐፊው ተናግረዋል።
ሊቀ ትጉሃን “መንግሥት የመንግሥትን ሚና እንዲጫወት እንደ እምነት ተቋማት እያሳሰብን ነው፤ በተለይ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ ሰፊ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል” ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማትም ከምንግዜውም በላይ በጋራ እሴቶቻቸው ላይ ጠንክረው ተከታዮቻቸውን ማስተማር እንደሚገባቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ጽሐፊው፤ በተለይ አብሮነታቸው ላይ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።