
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 9/2012 ዓ.ም (አብመድ) የእምቦጭ አረምን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ በተዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት ውይይት ተደርጓበታል።
ስትራቴጂክ ዕቅዱ አረሙን ማስወገድ፣ በዘላቂነት የውኃና አካባቢ ጥበቃ መሥራትና ነፃ የሀይቅ ዳርቻ መሥራት እንዲሁም በሀይቁ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
በዕቅዱ ላይ ገለጻ ያደረጉት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶክተር ኢንጂነር) የእምቦጭ አረም በ1956 ዓ.ም በአባ ሣሙዔል ግድብ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ መጤ ወራሪ አረም መሆኑን አስታውሰዋል።
ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በጣና ሀይቅ ላይ አረሙ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑንና በሰባት ወረዳዎችና 35 ቀበሌዎች መዳረሱንም ተናግረዋል።
እምቦጭ አረም በብዝሃ ሕይወት አንዲሁም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ የደቀነው ሥጋት ከፍተኛ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በጣና ሀይቅና በአጠቃላይ በጣና ተፋፈስ ዙሪያ የእርሻ መስፋፋት፣ የውኃ አካላት ላይ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች፣ ከከተማና ከኢንዱስትሪ ወደ ጣና ሀይቅ የሚገቡ ፍሳሾች አረሙ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
ይሁንና አረሙን ማስወገድ የሚቻለው ልማዳዊ ከሆነ አሰራር ወጥቶ ስትራቴጂውን ተግባራዊ በማድረግ መሆኑን በመግለፅ ለዚህም በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የተለያዩ አገሮችን ተሞክሮች በማየት እምቦጭ አረምን ለኃይል አማራጭነት መጠቀም እንደሚቻል መግለፃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
የእምቦጭ አረምን ለመከላከል በጣና ተፋፈስ ዙሪያ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ በተለይም የተለያዩ ፈሳሾችና ንጥረ ነገሮች ወደ ሀይቁ እንዳይገቡ የማድረግ ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።