
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 9/2012 ዓ.ም (አብመድ) በናይል ተፋሰስ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ታላቁ የሕዳሴ ግድብን የተመለከተ የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በውይይቱ የተሳተፉት በናይል ተፋሰስ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ወገኖች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ቦንድ በመግዛትና በቴክኒክ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
“ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ ሁለት ሶስተኛ የሆነውን ውሃ የምታበረክት በመሆኑ ተፋሰሱን የማልማት ጉዳይ የሀገርን ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የሕዝብን የዘመናት የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ቁልፍ ሚና ይጫወታል” ብለዋል ሚኒስትሩ። የግድቡ መጠናቀቅ ከኢትዮጵያ አልፎ ለተፋሰሱ ሀገራት እና ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ፈር ቀዳጅ ፕሮጀክት መሆኑንም አቶ ገዱ ለተሳታፊዎቹ አስረድተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ እስካሁን ላበረከቱት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ አመስግነውም በግድቡ ላይ በያሉበት የኢትዮጵያ አምባሳደርነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። ይህም በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የጠራ የጋራ ግንዛቤና አቋም እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
ኬንያን ጨምሮ በውይይቱ በተፋሰሱ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመወከል የድጋፍ መልዕክት ያስተላለፉት ተሳታፊዎች ቦንድ ለመግዛትና ዲፕሎማሲያዊና የቴክኒክ ድጋፍ ሐማሰባሰብ እንዲሁም ሰፊ የገጽታ ግንባታ ሥራ ለመስራት ቃል ገብተዋል። መንግስትም ፕሮጀክቱን በብቃት በመምራት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ በማድረጉ አመስግነዋል።
በፓናል ውይይቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና የሦስትዮሽ ድርድር ሂደት ውስጥ ታላቅ ሚና ከሚጫወቱት ባለሙያዎች መካከል ያቆብ አርሳኖ (ዶክተር) እና ጌዲዮን አስፋው (ኢንጂነር) እንዲሁም አቶ ዘርይሁን አበበ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበዋል።
በኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ግብጽ፣ ጅቡቲና ሶማሊያ የሚገኙ የሚሲዮን መሪዎችና ዲፕሎማቶችም በፓናል ውይይቱ መሳተፋቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስነብቧል።