
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 8/2012 (አብመድ) የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በ2012 በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 737 ሺህ 506 ዶላር ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታውቋል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ከ42 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም ኤጀንሲው ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንደገለጹት ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ የዳያስፖራው ድጋፍና ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል። የግድቡ ግንባታ ሂደት የነበሩበት ችግሮች ተወግደው በተሻለ ሁኔታ እየተከናወነ በመሆኑ እና የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌቱም መካሄዱ ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩንም ገልጸዋል።
በ2012 በጀት ዓመት የዳያስፖራ ማኅበረሰብ 737 ሺህ 506 ዶላር ድጋፍ ማድረጉንም ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የገለጹት።
ኢዜአ እንደዘገበው በአጠቃላይ የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በዳያስፖራው በኩል ከ42 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።
በ2013 በጀት ዓመት ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 200 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ከ13 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ እንደተሰበሰበ እና ከዚህ ውስጥ የዳያስፖራው ድርሻ 1 ቢሊዮን 6 ሚሊዮን ብር መሆኑን ኤጀንሲው ገልጿል።