
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 8/2012 ( አብመድ) ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ከታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር እያካሄደችው ያለው ድርድር በሌሎች ወንዞቿ ላይ የልማት ሥራዎችን በቀላሉ እንድታከናውን የሚያስችል መሠረት ጥሎ ማለፍ እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች አመላከቱ።
የግድቡ ግንባታ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የነበረውን የተሳሳተ ምናባዊ ትንተና እንደቀየረ ባለሙያዎቹ አንስተዋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ከጥንት ጀምሮ ፍትሃዊና ሚዛናዊ አቋም መያዟን ገልጸዋል። ይሁንና በተለይ የታችኞቹ የወንዙ ተፋሰስ አገሮች ኢትዮጵያ ውድቅ ያደረገቻቸውን የቅኝ ግዛት ውሎች ጭምር እንድትቀበል የሚያደርጉት ጥረት የአገሪቷን ብሄራዊ ጥቅም የሚገዳደር በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።
የድርድር ሂደቱ ኢትዮጵያ ወንዞቿን አልምታ መጠቀም በሚያስችላት መልኩ መካሄድ እንዳለበትም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ድርድሮች በዓባይ ወንዝም ሆነ በሌሎች ወንዞች ላይ ለሚሰሩ የልማት ስራዎች ጥያቄ በማያስነሳ መልኩ መሠረት ጥለው ማለፍ እንዳለባቸውም አመላክተዋል። የምክክር፣ የጥናትና የትብብር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አብደታ ድርብሣ (ዶክተር ) የአባይ ግድብ በአፍሪካ የ2063 አጀንዳዎች ላይ ከተቀመጡ ጉዳዮች አንዱ መሆኑንና የበርካታ አፍሪካውያንን ሕይወት ይቀይራል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል። ከግብጽና ሱዳን ጋር እየተካሄደ ያለው ድርድርም ኢትዮጵያ ለመልማት የምታደርገውን ጥረት በማያደናቅፍ መልኩ ማስቀጠል እንደሚገባው አክለዋል።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የዲፕሎማሲ ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴ በበኩላቸው “የግድቡን ግንባታ መጀመር ነበር ከባዱ፣ ያን እርምጃ አልፈነዋል” ብለዋል። ይህም በራስ አቅም ትልቅ ነገር መሥራት እንደምንችል፣ የወንዞች፣ የልማት፣ የትምህርትና ሌሎች ሥራዎችንም መሥራት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ጌታቸው መኮንን የሦስቱ አገራት ድርድር አድካሚና እልህ አስጨራሽ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ተደራዳሪዎቹ ባደረጉት ትግል ኢትዮጵያ ወደ ምትፈልገው፣ ፍትሃዊና ሚዛናዊ አጠቃቀም መሸጋገሩን አንስተዋል።
ባለሙያዎቹ ግድቡን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ድርድርና ውይይቱ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ብቻ ሳይወሰን ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች ጋርም መካሄድ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን እያከናወኑት ያለው ድርድር እስካሁን መቋጫ አላገኘም።
የግድቡ አጠቃላይ ግንባታም አሁን ላይ 75 በመቶ ላይ ደርሷል። በመጀመሪያው ዙር 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዲይዝ ተደርጓል።
በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ በግድቡ ሁለት ተርባይኖች ሃይል የማመንጨት ሙከራ እንደሚደረግም ይጠበቃል።