“ከፊል ደስታ ከፊል ሐዘን ላይ ብንሆንም ደስታችን አመዝኗል።” የኢንጂነር ስመኘው ቤተሰቦች

244

ትንናት ቅኔ፣ ዛሬ ደምና ወኔ የሆነን ዓባይ በጉባ ሰማይ ሥር በሀገሩ መሬት አርፎ እንዲሄድ ሲታቀድ የውሃውን ማደሪያና መሰንበቻ ቤት የሚሠራ አንድ ጠቢብ ሰው አስፈልጎ ነበር፡፡ ዓባይ በሀገሩ ሊያድር ቤት የሚሰራለትም የሀገሩ ልጅ ብቻ ነበር፡፡ የሚሰራው ሥራ መልዕክቱ አንድ ብቻ አልነበረም፡፡ የሀገርንና የሕዝብን አደራ መሸከም ግድ ይል ነበር፡፡ አደራው እንዲሁ በቀላሉ የሚታይም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን እናቶች ከመቀነታቸው እየፈቱ ከጉያቸው ሥር እያወጡ በሰበሰቧት ሳንቲም ውስጥ ተስፋ፣ እመነት፣ ፍቅርና አንድነትም አብረው ሰጥተዋልና፡፡

ያን አደራ የሚቀበለው ሰውም በምድጃ አጠገብ ተቀምጠው ጭስ አቅላቸውን እያሳታቸው ቃል ያስገቡትን እዳ ነበርና ነገሩ ያስፈራል፤ ያስደነግጣልም፡፡ በሌላ ደግሞ ሚሊዮን እናቶችን ከጨለማ አውጥቶ በኢትዮጵያውያን የተጣለበትን የእምነት እዳ ተወጥቶ በሕዝብ አደባባይ ሲደሰት ማዬትም ሌላ ተስፋ ነበር፡፡ ለዘመናት ታልሞ ሳይሳካ የቆየውን የዓባይ ማደሪያ በበላይነት መሥራት ከሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መካከል ለአንድ እድለኛ መሰጠት ያስፈልግ ነበርና ከሚሊዮኖች የተመረጠው በኃላፊነት ተረከበው፡፡ ለዚህ የተመረጡትም ኢንጂነር ስመኛው በቀለ ነበሩ፡፡

ዓባይ በሀገሩ ምድር እንዲሰነብት ኢትዮጵያውያን ተስማሙ፡፡ በወረሃ መጋቢት የማረፊያ ቤቱ ሊሰራለት የመሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ፡፡ ኢትዮጵያውያን ጮቤ ረገጡ፡፡ ሁሉም ዓባይ ላይ ዘመተ፤ ሥራውም ተጀመረ፡፡ ከሚሊዮኖች የተመረጡት የግድቡ ሥራ አስኪያጅም በጭስ ተደብቀው አደራ ያሏቸውን ኢትዮጵያዊያንን ድምጽ በእዝነ ልቦናቸው እያዳመጡ ከቤተሰብ ተለይተው ወደዚያ በረሃ ወረዱ፡፡

ታላቁ ሰው ከቤተሰብ ርቀው፣ እንደ ሌሎች አባቶች ከልጆቻቸው ጋር ሳይጫወቱ፣ ቀዝቀዝ ባለ አየር ሳይናፍሱ አደራቸውን ለመወጣት ኳተኑ። በኢትዮጵያውያን ታምኖ ጎድሎ መገኜት ከባድ ነበርና የራሳቸውን ደስታ ወደ ጎን ትተው የአገርን ደስታ ለማስቀደም ደከሙ፡፡ ከሙያ አጋሮቻቸውና ከኢትዮጵያውያን ጋር ሆነው ከመሠረት አንስተው ሥራውን ከፍ አደረጉ፡፡

ዳሩ ግን የጀመሩትን መቋጨት አልቻሉም፡፡ ሥራውን ጨርሰው ይሞገሱበታል በተባለው አደባባይ ላይ ሕይወታቸው አልፎ ተገኙና ኢትዮጵያዊያን ደነገጡ፡፡ ሀዘኑም ከፍ አለ፡፡ ከሁሉም ግን ከጉባ በረሃ ተመልሰው ፍቅር እስኪሰጧቸው ሲጠባበቁ ለነበሩ ቤተሰቦቻቸው ሐዘኑ ከባድ ነበር፡፡ በሀሩር ሥር የተደበቀን መብራት ፈንጥቀው በጨለማ ውስጥ የኖረውን የኢትዮጵያዊ ለማስደሰት የጀመሩት ውጥን መስቀል አደባባይ ላይ ተቋጨ፡፡ ለኢትዮጵያውያንም የተጀመረ ሥራ፣ የጎመራ ፍቅር፣ የተባ አንድነት፣ ከፍ ያለ መተሳሰብ ትተው እንዲጨርሱት በመንፈስ አበርትተው በአንደበታቸው ሳይሰናበቱ ላይመለሱ አሸለቡ፡፡

የኢትዮጵያውያን ተስፋ በስሎ ሳያዩት፣ አብርቶ ሳይመለከቱት በጎን የሀገር ፍቅር፣ በጎን ደግሞ የቤተሰብ ፍቅር እንዳቃጠላቸው፤ በላይ የጉባ በረሃ እንደገረፋቸው ወደማይቀርበት ተሰናበቱ፡፡
ኢንጂነር ስመኘው ለዘመናት የተመኘነውንና የተመኙትን ፈፅመው ባያሳዩንም የማይደፈር ደፍረው፣ ያልተጀመረ አስጀምረው አጋምሰው ጥለውት ስለሄዱ የተጀመረው አልቆመም፤ ሥራው ቀጠለ፡፡ የዓባይ ግድብ ገና ሲታለም አንስቶ ከፍ ያለ ግምት ቢሰጠውም በተለይም ግን በቅርብ ዓመታት የዓለም አቀፍ አጀንዳ፣ የአንድነት፣ የጽናት እና የጀግንነት መለኪያ፣ የዜግነት መፈተኛ ሆኗል፡፡ ግብፅ አትንኩብኝ፣ ኢትዮጵያም በጋራ እንጠቀም ስትል የባለቤቱና የጎረቤቱ ውይይትና ድርድር ቀልብ ሳበ፡፡

የሽያጭ ፍንጥር ለመጠጣት የቋመጡ የሚመስሉ ጥቂቶችም የዓባይን መሸጥ በአደባባይ “ሲያበስሩ” ሰነበቱ፡፡ ሥራው እየቀጠለ፣ ድርድሩም እየተካሄደ ባለበት ጊዜ የዓባይ ውሃ ከጉዞው ማረፍ ጀመረ፡፡ በጉባ መሬት ላይ ተኝቶ እንደ ወዳጁ ጣና ፈልሰስ ብሎ ተኛ፡፡

ቢዘያ ስፍራ ውሃ ብቻ ሳይሆን የተሞላው፣ ታሪክ፣ ክብር፣ ሉዓላዊነትና አንድነትም ጭምር ነውና በውጥረት መካከል የዓባይ ውሃ የመጀመሪያ ሙሌት መጠናቀቀቅ ሲሰማ ኢትዮጵያዊነትን ለሚወዱ ኢትዮጵያዊያን ደስታው እጥፍ ድርብ ሆነ፡፡ የሽያጭ ፍንጥር ለመጠጣት ሲቋምጡ የነበሩትም አፈሩ፡፡ ማንነው ወንዱ ሲሉት የነበሩትም ደነገጡ፡፡

ይህ የኢትዮጵያውያን ደስታ በፍቅር መምጣታቸውን ሲጠባበቁ ለነበሩ የኢንጂነር ስመኘውስ ቤተሰቦችስ ምን ያክል ይሆን ?

በእምነት ስመኘው የኢንጂነር ስመኘው የመጀመሪያ ልጅ ነው፡፡ ከአብመድ ጋር በስልክ በነበረው ቆይታ “የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁ በጣም ትልቅ ደስታ ነው የተሰማን፡፡ በእርግጥ የተለፋበት ነገር ነው፡፡ እንደዚህ ዳር ይዞ ማዬቱ በጣም ደስ ይላል፡፡ ቤተሰብ በሙሉ ደስ ብሎናል፡፡ በእርግጥ አርሱ ቢኖር የበለጠ ደስ ይለን ነበር፡፡ ቢያዬው የሚለው ነው እንጂ ከዚያ ውጭ ያለው በጣም ነው ደስ የሚል፡፡ እኛም በተቻለን መጠን ግድቡ እንዲጠናቀቅ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብን ይህንኑ ነው ማድረግ ያለበት፡፡ የጋራ ዓላማ ኖሮን በአንድነት ታላቅነትን ለማሳካት መሄድ አለብን፡፡ ለኢትዮጵያውያንም የማስተላልፈው መልዕክት ይህንኑ ነው ” ብሏል፡፡ በዓባይ ጉዳይ የሚነሱትን አሉባልታዎች መሥማት እንደማይገባና በጋራ መቆም እንደሚያስፈልግም ተናግሯል።

የኢንጂነር ስመኘው የባለቤቱ እናት መንበረ መኮንን “የግድቡ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ትልቅ ድል እንደሆነ ይሰማናል” ነው ያሉት፡፡ “በእርግጥ ቆሞ ባለማዬቱ አዝነናል፤ ለእኛ ሁለት አይነት ነው ስሜቱ፤ ማዘንም አለ፤ መደሰትም አለ፤ ነገር ግን ደስታው ያመዝናል” ብለዋል፡፡ ጨርሶት ስላላዬን አዝነናል፤ ነገር ግን ሀዘናችን በዚህ በመካሱ ደስ ብሎናልም ብለዋል፡፡ ስለዓባይ የሚነገሩ አሉባልታዎች ሊሆኑ የማይችሉ በመሆናቸው ሕዝቡም ሊቀበላቸው አይገባም ብለዋል፡፡ ይህች አገር የምትሄድበትን መልካም ነገር መከተል እንጂ ሕዝብን ሌላ ሀሳብ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡

“አሁን ላይ ተስፋ የሚሰጥ መልካም ነገር አለ፤ የግድቡ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም፤ ለዚህ ግድብ ስመኘው ብዙ መስዋዕት ከፍሎበታል፡፡ ይህ ሲያልቅ ነው የበለጠ ደስ የሚለን” ነው ያሉት፡፡ የግድቡን መሞላት በሰበር ዜና ሲያወጡ የነበሩ መገናኛ ብዙኃን ኢንጂነር ስመኘውን አለማንሳታቸው እና በቤተሰቡ ዘንድ የተፈጠረውን ደስታ አለመጠዬቃቸው እንዳሳዘናቸውም ተናግረዋል፡፡ በሙሌቱ የደስታ ቀን ኢንጂነር ስመኘው መታወስ እንደነበረባቸውም ነው በቅሬታ የተናገሩት፡፡ የኢንጂነር ስመኘው መታሰቢያ ሀውልትም በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ አቅራቢያ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከዓመታት በፊት ኢንጂነር ስመኘው የተቀበሉት አደራ በተከታዮቹ ቀጥሏል፡፡ አንድ ሆነን እንደ ጀመርነው አንድ ሆነን ከሠራነው፣ አንድ ሆነን እንደሰትበታለን፤ ብርሐንም ይሆነናል።

በታርቆ ክንዴ

Previous articleበኩዌት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድ ሳምንት ብቻ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ መግዛታቸውን ኤምባሲው አስታወቀ።
Next articleየሕዳሴ ግድብ ድርድር ኢትዮጵያ በወንዞቿ ላይ የልማት ሥራዎችን በቀላሉ ማከናወን እንድትችል መሠረት ጥሎ ማለፍ እንዳለበት ባለሙያዎች አመላከቱ።