ሩሲያ ይፋ ያደረገችው ክትባት ውጤታማ ስለመሆኑ አለማረጋገጡን ዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

207

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 8/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአዲስ ተገኘ በተባለው የኮሮናቫይረስ ክትባት ጉዳይ ከሩሲያ ጋር እየተወያየ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ሩሲያ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል መወሰኗን ይፋ ማድረጓ ይታወሳል። ከ20 በላይ ሀገራት 1 ቢሊዮን ብልቃጥ ክትባት ማዘዛቸውንም ሞስኮ ገልጻለች።

የዓለም ጤና ድርጅት ደግሞ በክትባቱ ላይ ተጨማሪ መረጃ እንደሚያስፈልገው ገልጿል። በመረጃው መሠረት የቀጣይ ሂደት እንደሚወሰንም አስታውቋል።

ከአለም ጤና ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከ 170 በላይ የኮሮናቫይረስ ክትባቶች የተለያዩ የግምገማ ደረጃዎችን አልፈዋል። ከእነዚህ ውስጥ 26 የሚሆኑት በሕክምና የሙከራ ሂደት ላይ የሚገኙ ናቸው። ቀሪዎቹ ደግሞ በቅድመ የሕክምና ሙከራ ሂደት ላይ ይገኛሉ።

ከሰሞኑ በዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛዎች ሰፊ ሽፋን የተሰጠው ሩሲያ ጥቅም ላይ ያዋለችው አዲስ ክትባትም በሕክምና የሙከራ ሂደት ላይ ካሉት መካከል የተካተተ ነው።

ክትባቱ ውጤታማ ስለመሆኑ በዓለም ጤና ድርጅት ያልተረጋገጠ መሆኑ ተመላክቷል። የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ብሩስ ባስተላለፉት አጭር የቪዲዮ መልዕክት ስለ ክትባቱ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማጠናቀር፣ የሙከራ ሂደቱ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ እና የተገኘውን ውጤት ለመረዳት ከሩሲያ መንግሥት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። ከውይይቱ በኋላም ቀጣይ መደረግ የሚገባቸው ጉዳዮች እንደሚወሰኑ ከፍተኛ አማካሪው ገልጸዋል።

ሩሲያ የመጀመሪያውን ክትባት ማግኘቷን ለመግለጽ ችኮላ እንደታየባትም አናዶሉ ዘግቧል። የኮሮናቫይረስን ስርጭት ውጤታማ በሆነ መልኩ መከላከል የሚያስችል ክትባት ከተገኘ የዓለም ጤና ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አመላክቷል።

እንደ አናዶሉ ዘገባ ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን ለማፋጠን የዓለም ጤና ድርጅት የማበረታቻ መርሃ ግብር አለው፤ ነገር ግን የክትባቱ ምቹነት እና ውጤታማነት እንዲታወቅ የሚጠበቅበትን ሂደት ማለፍ ይኖርበታል።

በደጀኔ በቀለ

Previous articleጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም የሚያስችል የአምስት ዓመት የድርጊት መርሃ ግብር መዘጋጀቱን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
Next articleበኩዌት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድ ሳምንት ብቻ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ መግዛታቸውን ኤምባሲው አስታወቀ።