ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም የሚያስችል የአምስት ዓመት የድርጊት መርሃ ግብር መዘጋጀቱን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

1211

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 8/2012 ዓ.ም (አብመድ) በክልሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ የተዘጋጀውን የአምስት ዓመት ፍኖተ ካርታ አስመልክቶ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ነሐሴ 8/2012 ዓ.ም ውይይት እንደሚካሄድ ቢሮው አስታውቋል።

በቢሮው የሴቶች ንቅናቄ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ስማቸው ዳኘ እንደገለጹት በክልሉ የህፃናት ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛት እና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በስፋት ይፈፀማሉ። ችግሩን ለማስወገድ የተለያዩ ሥራዎች ቢከናወኑም የተጠበቀውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ልጃ ገረጆችን አስመልክቶ በ2014 ( እ. አ.አ) እንግሊዝ ለንደን በነበረው መድረክ በተለይም በልጅነት ጋብቻ እና በሴት ልጅ ግርዛት ኢትዮጵያ ተወቃሽ እንደነበረችም አቶ ስማቸው አስታውሰዋል። ይህን ተከትሎም መንግስት በ2017 ዓ.ም እነዚህን ድርጊቶች ለማስቆም ቃል መግባቱን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ከ2012 እስከ 2016 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም የሚያስችል ሀገራዊ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል። ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ተከስተው በነበሩ ወቅታዊ ችግሮች በ2012 ዓ.ም ወደ ተግባር አለመገባቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ፍኖተ ካርታው ካለፋ ችግሮች በመነሳት የወደፊት ስትራቴጅዎችን፣ ስልቶችን፣ የክትትል እና የድጋፍ ሂደቶችን ያካተተ መሆኑን ነው አቶ ስማቸው ያስረዱት።

በውይይቱ 60 የሚሆኑ የክልል እና የዞን የሥራ ኃላፊዎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ይሳተፋሉ።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

Previous articleበኩር ጋዜጣ ነሐሴ 04/2012 ዓ/ም ዕትም
Next articleሩሲያ ይፋ ያደረገችው ክትባት ውጤታማ ስለመሆኑ አለማረጋገጡን ዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።