
ደብረታቦር: ሚያዝያ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በደብረ ታቦር ከተማ የሚገኙ በብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ አባላት በበጎ ፈቃድ ባሠባሠቡት ገንዘብ ለአቅመ ደካሞች የማዕድ ማጋራት መርሐግብር አካሂደዋል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ወጣቶቹ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ አስተምህሮዎችን መሠረት በማድረግ ያከናወኑት ተግባር የሚበረታታ መኾኑን ገልጸዋል።
የትንሣኤ በዓል ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገሪያ እና ሰው ሁሉ በአዲስ መንፈስ በዓሉን ሲያከብር አቅም የሌላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች አብረው በዓሉን እንዲያከብሩ ማድረግ በዓሉን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል ነው ያሉት።
በማዕድ ማጋራቱ ላይ የተገኙት የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮነን ደግሞ በዓሉ በዓል መኾኑ የሚታወቀው ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት ሲኾን እንደኾነ ጠቁመዋል። ወጣቶቹ እያደረጉት ያለው በጎ ተግባርም እጅግ ደስ ይላል ነው ያሉት።
የእቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ የወጣቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ተመስገን ወርቁ ረዳት የሌላቸው እና በራሳቸው አቅም በዓሉን ለመዋል የሚቸገሩትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በመለየት እገዛ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ወጣቶች በዓሉ ከመድረሱ በፊት ገንዘብ ከኅብረተሰቡ የማሠባሠብ ተገባራትን ሲያከናውኑ እንደቆዩም ነው የተናገሩት።
ኅብረተሰቡ አቅም የሌላቸው ወገኖች በዓልን በደስታ እንዲውሉ ያደረገው ድጋፍ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ከተሳታፊ በጎ ፈቃደኞች መካከል ወጣት ትግስት ጌትነት ከሠሩት የበጎ ተግባር ትርፋቸው የህሊና እርካት ብቻ መኾኑን ተናግራለች።
አቅመ ደካሞች ሳይከፋቸው በዚህ ማዕድ ሲጋሩ ለሀገር ፀሎት በማድረግ የድርሻቸውን ሲወጡ ማየት ከህሊና በላይ መኾኑንም ገልጻለች።
ይህ ተግባር የአንድ ቀን ብቻ ሳይኾ የሁልጊዜ ሥራ ኾኖ መቀጠል እንዳለበትም ነው የተናገረችው።
ማዕድ የተጋሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወጣት በጎ ፈቃደኞች ከጎናቸው ባይኾኑ ኑሮ እጅግ ያዝኑ እና ይከፋቸው እንደነበር ነው የገለጹት። ለተደረገላቸው ድጋፍም አመሥግነዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
