
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ውስጥ በ100 ሚሊየን ብር ወጪ የሚገነባው ‘ዳር ሀረር’ የመልሶ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ በአፋጣኝ ወደ ስራ ማስገባት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።
ፕሮጀክቱ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል አለም አቀፍ ቅርስን ለነዋሪውና ለጎብኚዎች የበለጠ ምቹ ለማድረግ የሚያግዝ ስለመሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱ ላይም የ”ዳር ሀረር” የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት የሀገር ኩራት ከሆነው የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ ታሪክና ይዘት ጋር በማጣጣምና የጀጎል ባህላዊ የግንባታ ጥበብን በተከተለ መልኩ የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል።
በሚገነባው የ”ዳር ሀረር” የመልሶ ማልማት ፕሮጀክትም በቅርሱ ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎችን ህይወት ለማሻሻል የሚያግዝ መሆኑ ተጠቅሷል።
ፕሮጀክቱ ሕዝብን ተጠቃሚነት ከማሳደግም ባሻገር የሀረርን ከፍታ ለማረጋገጥ በሚሠሩ ሥራዎች የጎላ ፋይዳ እንዳለው ነው የተመላከተው።
በፕሮጀክቱም ዘመናዊ አገልግሎት የሚሰጡ ታሪካዊ ይዘታቸውን የጠበቁ የቱሪስት ማረፊያዎች እንደሚገነቡም ከሀረር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም ሀረርን በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የቅርስ ቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው የተገለጸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
