ትውልዱ እንደ ዳክረስ ልቡ የደነደነ መኾን የለበትም።

5
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በስቅለተ ዓርብ ከሚታወሱ ሁነቶች መካከል በኢየሱስ ክርስቶስ ግራ እና ቀኝ የተሰቀሉት የሁለቱ ወንበዴዎች ታሪክ አንዱ ነው።
በማኅበረ ቅዱሳን መቅረዝ ትምህርት ቤት የግዕዝ እና የግብረገብ መምህር የኾኑት ሰናይ ደጉ ለአሚኮ እንደገለጹት በቀኝ የተሰቀለው ጥጦስ ሲኾን በግራ በኩል የተሰቀለው ደግሞ ዳክረስ ይባላል ብለዋል።
ጥጦስ የሚለው ስም ትርጓሜ ተመለሰ ወይም ተጸጸተ ማለት ሲኾን ዳክረስ ደግሞ በሠራው ክፉ ተግባር ወደ ሲኦል መውረዱን የሚያመለክት ስያሜ እንደኾነ ገልጸውልናል።
እነዚህ ወንበዴዎች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸው ታሪክ የሚጀምረው በስቅለቱ ዕለት ብቻ ሳይኾን ከገሊላ ጀምሮ ነው ብለዋል። ሁለቱም በአይሁድ ምድር ግፍን ሢሠሩ የኖሩ ጨካኝ እና አረመኔ ወንበዴዎች እንደነበሩም ጠቁመዋል።
ጌታ በመስቀል ላይ በተሰቀለበት ወቅት ሰባት ተአምራት ተከናውነዋል ነው ያሉት። በቀኝ በኩል የተሰቀለው ጥጦስ እነዚህ ተአምራት ተገልጠውለት በማስተዋሉ ልቡ ወደ ንስሐ ተመልሷል።
በዚህም “አቤቱ ጌታ ኾይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” በማለት ምሕረትን ተማጽኗል ነው ያሉት። ጌታም “እነሆ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ” የሚለውን የተስፋ ቃል እንደሰጠው አስረድተዋል።
በተቃራኒው በግራ በኩል የተሰቀለው ዳክረስ ልቡ እንደ አይሁዳውያን የደነደነ በመኾኑ አልተጸጸተም ብለዋል። ይልቁንስ “አምላክ ከኾንክ አንተንም እኛንም ከስቅላት አድነን” እያለ ይዘባበት ስለነበር የሲኦል በር መክፈቻ ምሳሌ ኾኗል ይላሉ።
የሁለቱ ወንበዴዎች በግራ እና በቀኝ መሰቀልም በፍርድ ቀን ጻድቃን በቀኝ ኃጥአን ደግሞ በግራ የሚቆሙ መኾናቸውን የሚያመሰጥር መኹኑን ገልጸውልናል።
ጥጦስ የጻድቃን፣ ዳክረስ ደግሞ የኃጥአን ምሳሌ ተደርገው ይወሰዳሉ ነው ያሉት።
“የዛሬው ትውልድ እንደ ዳክረስ ልቡ ከመጨከን ወጥቶ እንደ ጥጦስ በንስሐ ወደ በጎ ተግባር መመለስ እንደሚገባው” መምህር ሰናይ ደጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየእርድ እንስሳት ገበያን ለማረጋጋት እየተሠራ ነው።
Next article“ማርያም አዘነች፤ አብዝታም አለቀሰች”