
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዛሬ ባለታሪካችን በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ጎንጅ ቆለላ ወረዳ የአዲስ ዓለም ከተማ ነዋሪ የኾኑት አባት ናቸው።
ለረጅም ዓመታት አካባቢያቸውን በሰላም አስከባሪነት ሲያገለግሉ ኖረዋል፤ ዛሬም እያገለገሉ ይገኛሉ።
ነገር ግን ከሰሞኑ መጋቢት 27/2018 ዓ.ም የተከሰተው ግጭት የገንዛ ልጃቸውን ነጥቆ የልብ ስብራትን አስከትሎባቸዋል።
ቤተሰባቸውንም የሀዘን ማቅ አልብሶባቸዋል። እኒህ አባት ለአሚኮ ዲጂታል እንደተናገሩት ልጃቸው ተጨንቀው ያሳደጉት፣ ከራሱ አልፎ ለሀገር ይጠቅማል ብለው ከራሳቸው በላይ ይሳሱለትም እንደነበር አጫወቱን።
ቀድሞም ወደ ጥፋት መንገድ እንዳያመራ በተደጋጋሚ መከሩ፣ በሽማግሌዎችም አስመከሩ። ወደ ከተማ ገብቶ እንዲሠራ ደጋግመው ጠይቀውትም ነበር።
ወጣቱ ግን የአባቱን ምክር እና የቤተሰብ ፍቅር ወደ ጎን በመተው በሕገ ወጥ መንገድ ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሀሳብ ተወሰደ።
መጨረሻውም አባት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ግንባር ላይ ሲቆሙ ልጅ ደግሞ ባደገበት ቀዬ ላይ ጦር ሰብቆ ከሕገ ወጦች ጋር ተሰለፈ።
ለሕዝባቸው ሰላም የቆረጡ አባት እና በሕገወጦች ሀሳብ የተወሰደው ልጃቸው በሁለት ጎራ ለግጭት ተሰለፉ። በውጊያውም ልጃቸው ሕይወቱን አጣ።
“ልጄን ከራሱ አልፎ ለሀገር እንዲጠቅም ነበር ያሳደግኩት፤ ነገር ግን በተሳሳተ ዓላማ እና በጥፋት መንገድ ሄዶ አጥቼዋለሁ” በማለት በተሰበረ ስሜት አባት ገልጸውልናል።
በቁጭት የሚናገሩት እኒህ አባት ግጭቱ አስከፊ፣ አሸናፊ የሌለው፣ እርስ በርስ መገዳደልን ያመጣ ስለመኾኑም በልጃቸው የደረሰውን በቅርብ ማሳያነት ያነሳሉ። ቤተሰብን ከማጉደል ባለፈ የሀገርን ክብር እንደሚያዋርድም ያስገነዝባሉ።
በጫካ ያሉ ኃይሎችም ቆም ብለው በማሰብ ከተሰለፉበት የጥፋት መንገድ እንዲመለሱ በአጽንኦት መክረዋል።
ግጭት ይብቃ፣ ሰላም ይስፈን!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
