
ባሕርዳር፡ ሚያዝያ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የምሥራቅ ፀሐይ ጉባኤ ቤት የአራቱ ጉባኤያት የትርጓሜ መምህር ዘመላክ ዳግም ዕለተ አርብ ክርስቶስ የተሰቀለባት መኾኗን በማስታወስ ሦሥት ነገሮችን ማለትም ድኅነት፣ ሰላም እና ፍቅርን በማሰብ ዕለቷን ማክበር ያስፈልጋል ብለዋል።
እነዚህ ተግባራት ክርስቶስ የፈጸማቸው፤ ሰውም ሊፈጽማቸው የሚገቡ እንደኾኑ አስረድተዋል።
መምህሩ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ብዙ ፍዳ መክፈሉን ተናግረዋል። ያለ በደሉ ለሰው ልጆች በደል ሲል ተገርፎ፣ ተሰቃይቶ፣ ተሰቅሎ፣ መከራን ተቀብሎ የሰውን ልጅ ከዲያብሎስ ግዛት አላቋል፤ ከሲዖል ወደ ገነት፤ ከባርነት ወደ ጌትነት መልሶ ድኅነት እንዲያገኝ አድርጓልም ነው ያሉት።
በዚህም የስቅለት ዕለት “ዕለተ ድኅነት” ወይም “የመዳን ቀን” ትባላለች ነው ያሉት።
ፍቅር ክርስቶስን ከሰማዬ ሰማያት አውርዶ፤ ከዙፋኑ ዝቅ አድርጎ እስከ ሞት አደርሶታል ያሉት መምህር ዘመላክ በቆረሰው ሥጋው፤ ባፈሰሰው ደሙ ለአዳም ፍጹም ፍቅሩን የገለጸባት ዕለትም ናት ብለዋል። እለቷ “ዕለተ ፍቅር” ወይም “የፍቅር ቀን” ትባላለችም ነው ያሉት።
የበደለ አዳም፤ የተበደለ ክርስቶስ ኾኖ ሳለ እርሱ ግን ለአዳም ፍጹም ፍቅርን ገልጿል፤ ፍቅሩም ውለታ የለበትም ነው ያሉት። ሰውን ስንወድ ጥቅም ፈልገን ሊኾን እንደማይገባ እንዲኹም የበደሉንን ይቅር ማለት እና መውደድ እንዳለብንም የሚያሳይ መኾኑን ገልጸዋል።
ክርስቶስ ለሰው ልጅ ሲል ስጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ፍቅሩን ከገለጸ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባለው አማኙም ይህንን ፍቅር በሁሉም ሰው ላይ መፈጸም እንደሚገባው ነው ያነሱት።
ሌላው ክርስቶስ በዚህች ዕለት ሥጋውን ቆርሶ፤ ደሙን አፍስሶ ለዓለም የሰጠው ሰላም ነው ብለዋል። በደሙ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግድ አፍርሶ ዘላለማዊ ሰላም አምጥቷል፤ በዚህም የስቅለት ዕለት “ዕለተ ሰላም” ትባላለች ነው ያሉት።
የሰው ልጅም ክርስቶስ ዋጋ ከፍሎ የሰጠውን ድኅነት፣ ፍቅር እና ሰላም ገንዘቡ አድርጎ ሊኖር ይገባልም ብለዋል።
ክርስቲያኑ በየዓመቱ ዕለተ አርብ ወይም ስቀለት ሲመጣ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የከፈለውን ዋጋ በማሰብ ብቻ ሳይኾን ፍቅር እና ሰላም ገንዘቡ አድርጎ ማክበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል። ክርስቲያኑ ክርስቶስ ከበደሌ ይቅር ካለኝ፣ ካዳነኝ እና ከወደደኝ እኔ በዘመኔ ምን አደረኩ ብሎ ራሱን መጠየቅ እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
