ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው።

5
ባሕርዳር፡ ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ በሕገ ወጥ እና በሰበብ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እየወሰደ መኾኑን አስታውቋል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አትክልት አሳቤ ቢሮው የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የገበያ መሠረተ ልማት መሥራት እና ዘመናዊ የግብይት ሰንሰለት መዘርጋቱን ገልጸዋል። በዚህም ከደላላ ነፃ ግብይት እየተፈጠረ መኾኑን አንስተዋል።
አቅርቦት እና ፍላጎትን ለማጣጣም የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ ተሠርቷል ያሉት ምክትል ኀላፊዋ ከእሑድ እስከ እሑድ ገበያ እንዲኖር ይደረጋል ብለዋል። የኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ሸማቾች ምርት ካለበት በማምጣት ለማኅበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እንዲያደርጉ መደረጉን ተናግረዋል።
በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ማኅበረሰቦችን እስከ ዝቅተኛ ክፍያ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉንም አንስተዋል። ይህም ዓለማቀፋዊ ጫናን የማቃለል ድርሻው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል።
በሕገወጥ መንገድ እና በሰበብ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን አመላክተዋል። ይህንን ለመከላከል ቁጥጥር መደረጉንም ተናግረዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራትም በሕገወጥ ተግባር የተሰማሩ ከ103ሺህ በላይ ነጋዴዎች ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እና ሌሎች ወደ ዚህ ተግባር እንዳይገቡ ለማድርግ መሠራቱን አንስተዋል።
የምርት ጥራት ጉድለትን በመከላከል በኩልም ጊዜያቸው ያለፉባቸው ምርቶች እንዲወገዱ ተደርጓል ነው ያሉት።
ሕገወጥ ነዳጅ ጋር በተገናኘ በተሠራው የቁጥጥር ሥራ ከ662ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ መንግሥት ገቢ መደረጉን ነው የጠቆሙት። ይህም በገንዘብ ሲተመን ከ81ሚሊዮን ብር በላይ እንደኾነ ተናግረዋል።
ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እና ምርት በመደበቅ እጥረት ያለ በማስመሰል የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑንም ተናግረዋል። ለዚህም ማኅበረሰቡ ስግብግብ ግለሰቦችን ጥቆማ በመስጠት አጋር እንዲኾንም አሳስበዋል።
ዘጋቢ ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋሩ።
Next article“መሶብ፣ ፋይዳ እና ኮደርስ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ የሚያሳልጡ ናቸው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)