
ባሕርዳር፡ መጋቢት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መጋቢት 24 ቀን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ፣ በመንገድ መሠረተ ልማት ዘርፍ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ ይገኛል። በሐረሪ ክልልም ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የነዋሪዎችን የዓመታት ጥያቄ የመለሱ የልማት ሥራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።
ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በክልሉ የተከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች በከተማ እና በገጠር መካከል ፍትሐዊ የልማት ተደራሽነት እንዲኖር አስችለዋል።
በተለይም ገጠሩን ከከተማ ጋር የሚያገናኙ በርካታ የአስፋልት እና የጠጠር መንገዶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
ይህም አርሶ አደሮች ምርትን በቀላሉ ለገበያ በማቅረብ የእንግልት እና የምርት ብክነትን እንዲቀንሱ ረድቷቸዋል። ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኙ የመሠረተ ልማት አውታሮችም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን አነቃቅተዋል።
በከተማ ደረጃ የተገነቡ መንገዶች የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ከማሳለጥ ባለፈ ለከተማዋ ዘመናዊ ገጽታን አላብሰዋል። ምቹ የእግረኛ መንገዶች መገንባታቸውም የዜጎችን የደኅንነት ስጋት የቀረፈ እና የከተማዋን ውበት የጨመረ መኾኑ ተመላክቷል።
የለውጡ መንግሥት ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ጀምሮ በጥራት እና በፍጥነት ማጠናቀቅን ዋነኛ መገለጫው አድርጓል። በክልሉ እውን የኾኑት እነዚህ ፕሮጀክቶች ጊዜን ብቻ መሠረት ያደረጉ ሳይኾኑ ጥራታቸውን የጠበቁ እና ዘመን ተሻጋሪነትን ማዕከል አድርገው የተገነቡ መኾናቸውም ተገልጿል።
የሐረሪ ክልል መንግሥት የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ እና የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማስፋት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
