
ባሕርዳር፡ መጋቢት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሙነ ሕማማት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ በልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ትከበራለች። ምዕምናን በጾም፣ በስግደት እና በምስጋና የሚያሳልፏት ሳምንት ናት።
ከሕማም በኋላ የሚመጣው የትንሳኤ በዓል ደግሞ የሰላም እና የእርቅ በዓል ነው። የአብሮነት እና የመረዳዳት መንፈስም ጎልቶ ይታይበታል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በምሥራቀ ፀሐይ ይድበራ ማርያም ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ፣ የሐዲስ ኪዳን እና የፍትሐ ነገሥት መምህር ይኄይስ የሻምበል ከበዓሉ ቀደም ብሎ በተለይ በሕማማት ሳምንት የሚከናወነው ጾም እና ስግደት በተግባራዊ መረዳዳት ሊታጀብ ይገባል ብለዋል።
መረዳዳት በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይኾን በችግር ቀንም ሊጠናከር ይገባል። አንድ ሰው ካለው ላይ ቀንሶ ለወንድሙ ማካፈሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የላቀ ዋጋ እንደሚያሰጠውም አስገንዝበዋል።
በተለይ አሁን የሚታየው የትራንስፖርት ችግር ብዙዎችን ለመጉላላት እየዳረገ ነው ያሉት መምህር ይኄይስ ችግሩን ለመፍታት ተሽከርካሪ ያላቸው ወገኖች እግረኞችን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ ወቅት የትራንስፖርት ዋጋ መጨመሩም ለሕዝብ ፈታኝ መኾኑን ያነሱት መምህሩ የተሻለ አቅም ያላቸው ሰዎች የትራንስፖርት ወጭን ጭምር በመሸፈን ለበዓል ወደ ሌላ ቦታ የሚሄዱትን በማገዝ ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ነጋዴዎች እና ባለሀብቶች የዋጋ ንረቱን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለተቸገሩ ወገኖች ርህራሄ እንዲያሳዩም መክረዋል።
ሰላም የክርስትና አስተምህሮ መሠረት መኾኑንም ተናግረዋል። የእግዚአብሔር ሰው ኾኖ መምጣት እና መከራ መቀበል የሰላም ምንጭ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ፍቅር እና አንድነት በሌለበት የሚደረግ ጾም እና ጸሎት መንፈሳዊ ሙሉነት እንደማይኖረው ገልጸዋል። አማኞች ይቅርታን እና እርቅን በማስቀደም በዓሉን በሰላም እንዲያከብሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
