
ባሕርዳር፡ መጋቢት 28/2018(አሚኮ) በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ ኮር በሰሜን ጎጃም እና በደቡብ ጎንደር ዞኖች ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን የጽንፈኛ ቡድኑን ከፍተኛ መሪዎች ጨምሮ 90 የጽንፈኛ ታጣቂዎችን ከጥቅም ውጭ በማድረግ እና በመማረክ ውጤታማ አፈጻጸም ማስመዝገቡን አስታውቋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሩ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ እንደገለጹት ኮሩ ከመጋቢት 21/2018 ዓ.ም ጀምሮ በሰሜን ጎጃም (ሰሜን ሜጫ፣ ይልማና ዴንሳ፣ ጎንጂ ቆለላ፣ አዴት እና ባሕር ዳር ዙሪያ) እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ወረዳዎች ባካሄደው ዘመቻ 72 የጽንፈኛ ቡድን መሪዎች እና ተዋጊዎች ከጥቅም ውጭ ተደርገዋል ብለዋል።
በዚህ ኦፕሬሽን 14 ታጣቂዎች ተማርከዋልም ነው ያሉት። 28 የነፍስ ወከፍ እና 1 የቡድን መሣሪያ በቁጥጥር ሥር መዋሉንም ጠቁመዋል።
ጽንፈኛው ቡድን ገብቶባቸው የነበሩ ወረዳዎችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ተችሏልም ብለዋል።
በተለይ መጋቢት 27/2018 ዓ.ም በጎንጂ ቆለላ እና አዴት በነበረው ኦፕሬሽን ከጥቅም ውጭ ከተደረጉት መካከል ጽንፈኛው አዲስ ባጀራጀው የ33ኛ ክፍለ ጦር ወታደራዊ አዛዥ እና የ102ኛ ኮር ዘመቻ መሪ ሻለቃ ሸዋነህ ሙሉጌታ፣ የ33ኛ ክፍለ ጦር ልዩ ዘመቻ ኀላፊ ሃምሳ አለቃ ዘካሪያስ እና ይናገር ተገኘ የተባለ አመራር ይገኙበታል።
በተጨማሪም ስሙ ያልተጠቀሰ የክፍለ ጦር መረጃ ኀላፊ ፣ የብርጌድ ሎጅስቲክስ ኀላፊ እና ንብረት (ሸምሸም) የተባሉ መሪዎቹ ከጥቅም ውጭ ተደርገዋል።
ከሰሜን ወሎ የመጣው ታደለ፣ ከደቡብ ጎንደር የመጣው ማስሬ እና ከአማሪት የመጣው በቀለ ጌትነት በዚህ ኦፕሬሽን ከጥቅም ውጭ ተደርገዋል ብለዋል።
በዘመቻው የቡድኑ ሐኪም ጌትነት ተፈራ እና የሎጅስቲክስ ባለሙያው ሰውአለ ምኒችል ተማርከዋል ነው ያሉት።
ባለፉት ሰባት ቀናት በተደረገው ኦፕሬሽን ከቋራ ተነስቶ አዴት ሊደርስ የነበረ 1 ሺህ 344 ልዩ ልዩ ተተኳሾች ተይዘዋል። እንዲሁም ወደ ባሕር ዳር ሊገባ የነበረ 1 ሺህ 268 የመትረየስ እና 67 የድሽቃ ጥይት በወገልሳ አካባቢ በቁጥጥር ሥር ውሏል። ጽንፈኛው ከሕዝብ የዘረፋቸው አራት ተሽከርካሪዎችም ተመልሰዋል ነው ያሉት።
በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ እና ወገዳ ከተማ ሕዝብን ሲዘርፍ የነበረው ቡድን በድንገተኛ ኦፕሬሽን እንዲጸዳ ተደርጓል ብለዋል። በዚህም ማኅበረሰቡ በሰላም በመንቀሳቀስ የመንግሥት አገልግሎቶችን ማግኘት እንዲችል መደረጉን ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ አረጋግጠዋል።
አዛዡ አክለውም የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር እና የውስጥ ተላላኪ ባንዳዎችን ሴራ ለማክሸፍ ኮሩ ተልዕኮውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። ዘገባው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
