
ከሚሴ: መጋቢት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በከሚሴ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ የሰላም እና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ ከወጣቶች ጋር ምክክር ተካሂዷል።
በምክክሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። ወጣቶች ለሀገር አንድነት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ገልጸዋል።
አሁን ያለው ለውጥ የተጸነሰው በወጣቶች እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊው አሁንም ለሀገር ሰላም መረጋጋት የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅም ወጣቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ ወጣቶችን በልማቱ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ወጣቶች ለሰላም የበኩላቸውን በመወጣት የልማት ተባባሪ እንዲኾኑም እየተሠራ ነው ብለዋል።
የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም ወጣቶችን በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ከተማ አሥተዳደሩ ዕቅድ በማዘጋጀት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶችም ከመንግሥት ጎን በመኾን የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በከተማው በሚሠሩ ልማቶችም ወጣቶች በሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ ያደረጉ ናቸው ብለዋል። በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
