
ደሴ: መጋቢት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከ20ሺህ በላይ መምህራን እና የትምህርት መሪዎች የመምህራን የሙያ ፈቃድ ማረጋገጫ ምዘና እየወሰዱ ይገኛሉ።
የሙያ ፈቃድ ማረጋገጫ ምዘናው ወጥነት ያለው የመምህራን እና የትምህርት አመራር የሙያ ፈቃድ ማረጋገጫ የምዘና ሥርዓት በመዘርጋት ጥራት እና ብቃት ያላቸው መምህራንን ለማፍራት የሚያግዝ ነው ተብሏል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደምስ እንድሪስ የመምህራን እና የትምህርት መሪዎች የሙያ ፈቃድ ማረጋገጫ ምዘና ከዓመታት መቋረጥ በኋላ በቂ ዝግጅት ተደርጎበት እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል።
የምዘና ሂደቱ በክልሉ በ22 ዞኖች፤ በ171 ወረዳዎች እና በ146 የምዘና ጣቢያዎች ከ20ሺህ 452 በላይ ተመዛኞች ለማረጋገጫ የሚያበቃቸውን ፈተና እየወሰዱ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ምዘናው 75 ከመቶ ይዘት ላይ ሲያተኩር 25 ከመቶ ደግሞ የማስተማር ሥነ ዘዴ ዕውቀት ላይ ትኩረት ያደረገ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ውጤታማ፣ ብቁ መምህራንን እና የትምህርት መሪዎችን ለማፍራት ያለመው የምዘና ሂደት ግቡም የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል እና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ነው ብለዋል።
የምዘና ውጤቱ ከተተነተነ በኋላ በሚገኘው ውጤት ክፍተቶችን በመለየት መምህራንን በተለያዩ ሥልጠናዎች ለማብቃት በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
መምህራን እና የትምህርት መሪዎች ለሙያ ማረጋገጫ ምዘናው በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ደጀን አምባቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
