
ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ የምክክር መድረክ ከአልሚ ባለሃብቶች እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
የአማራ ክልል የግብርና ኢንቨስትመንት ማኅበር ኘሬዝዳንት መስፍን ክፍሉ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ37 ሄክታር መሬት አትክልት እና ፍራፍሬ እያለሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ዘርፉ ምርታማነትን በቀላሉ ከማሳደግ ባለፋ የኑሮ ደረጃን እንደሚያሻሽልም ገልጸዋል።
ከፀደይ ባንክ የመጡት ሙጨ ያለው ደግሞ ተቋሙ ምርታማነትን ለማሳደግ ለአልሚ ባለ ሀብቶች እና ለአርሶ አደሮች የመሬት ማረጋገጫ ደብተር በማስያዝ የብድር ፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረጉን ተናግረዋል። ብድር የመመለስ ችግርንም በጋራ ለመፍታት እና ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ያልታረሱ መሬቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደራሽ በማድረግ የተትረፈረፈ ምርት ለማምረት ያግዛል ነው ያሉት። ከምግብ ጥገኝት የሚያላቅቅ አሠራር መኾኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እብሬ ከበደ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመፍታት ውይይት መደረጉን ተናግረዋል። በክልሉ ከ1ሺህ 500 በላይ አልሚ ባለ ሀብቶች በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሠማራታቸውን አንስተዋል።
ከሀገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማምረት ክትትል እየተደረገ መኾኑን ያነሱት ምክትል ኀላፊው በክልሉ ከ200ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በግብርና ኢንቨስትመንት እየለማ መኾኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ልዩ አማካሪ ይትባረክ አወቀ ክልሉ በ25 ዓመት አሻጋሪ የዕድገት እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ከሚገኙ ጉዳዮች መካካል የግብርና ዘርፍን በማዘመን ምርታማነትን ማሳደግ ነው ብለዋል። የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፉን ማዘመን ምርት እንዲጨምር ከማድረጉ ባለፈ የክልሉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ድርሻው የጎላ መኾኑን አንስተዋል።
ወቅታዊ ችግሩ ፈተና ቢኾንም በዘርፉ የተሻሉ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለውጭ ገበያ የሚውሉ ምርቶችን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በግብርና ኢንቨስትመንት የተሠማሩ ባለሀብቶች ቴክኖሎጂ በመጠቀም ምርትን ከማሳደግ ባለፈ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚገጥማቸውን የፋይናንስ ችግር አበዳሪ ተቋማት ሊፈቱ ይገባል ነው ያሉት።
ግብርና ለሁሉም የኢኮኖሚ ምንጭ ነው ያሉት አማካሪው አስተማማኝ የምግብ ሉዐላዊነት ለመገንባት የግብርና ኢንቨስትመንትን በማዘመን መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
