
ከሚሴ: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሰንበቴ ከተማ እና ከጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) በአካባቢው ሰላምን ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች መኾኑን ጠቅሰዋል።
የነበሩ የአብሮነት እና የአንድነት እሴቶችን በማጠናከር ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር የተጀመረው ሥራም ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ለአትክልት እና ፍራፍሬ ኩታገጠም ምርት ምቹ በመኾኑ በመስኖ ልማት ላይ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ የጅሌ ጥሙጋ ሕዝብ ሰላሙን በማስጠበቅ ልማቱን እያፋጠነ ነው ብለዋል።
ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ቀጣናውን ሰላም በማድረግ ያደሩ መሬቶች እንዲለሙ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ማድረግ እንደተቻለም አስረድተዋል።
ከሰንበቴ ከተማ እና ከጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የተውጣጡ ነዋሪዎችም ከአጎራባች ወረዳ ወንድሞቻችን ጋር በጋራ እየተገበያየን እና የነበረንን የአብሮነት እሴት አጠናክረን እየቀጠልን ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
