መንግሥት ዜጎችን ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለማሽጋገር እየሠራ ነው።

5

 

ጎንደር: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምግብ ዋስትና እና ሴፍትኔት ጽሕፈት ቤት የልማት ተጠቃሚ ወገኖችን አስመርቋል።

‎የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምግብ ዋስትና እና ሴፍትኔት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሃድያ መሐመድ በከተማዋ ከ56ሺህ 600 በላይ የሴፍትኔት ልማት ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

‎ዛሬ ከ15ሺህ በላይ ተጠቃሚ ወገኖች መመረቃቸውንም አንስተዋል። ፕሮጀክቱ አቅመ ደካማ አረጋውያንን እየደገፈ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

‎በከተማው በፕሮጀክቱ የሚታቀፉ ዜጎችን ፍትሐዊ በኾነ መንገድ ለመመልመል ተገቢውን መስፈርት በማዘጋጀት ከመጀመሪያ ዙር ጀምሮ ከተጠቃሚ ክፍለ ከተሞች፣ ከቀበሌዎች እና ከቀጣናዎች ጋር ተሠርቷል ነው ያሉት።

‎”በቀጣይም ወደ ድህነት አዙሪት እንዳትመለሱ ያካበታችሁትን የሥራ ባሕል በማሳደግ እና የተሰጣችሁትን የሥራ ማስጀመሪያ ጥራት ለታለመለት ዓላማ በማዋል ኑሮአችሁን እንድታሻሽሉ የአደራ ጥሪየን አስተላልፋለሁ” ብለዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው መንግሥት ድህነትን ለማስቀረት የጀመረው የልማታዊ ሴፍትኔት መርሐ ግብር በርከት ያሉ ዜጎችን እየቀየረ መኾኑን ገልጸዋል።

‎ያገኛችሁትን የሥራ ባሕል ተጠቅማችሁ ለከተማው ልማት ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት።

‎ከተማ አሥተዳደሩ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾኑንም ተናግረዋል።

‎ሀገር የምትጸናው በምርጫ በመኾኑ ሀገርን ለማጽናት በሚሠራው ተግባር ሴቶች የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) መንግሥት ባለፉት ሦሥት ዓመታት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለማሽጋገር 60 ቢሊዮን ብር በመመደብ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

‎በአካባቢ ልማት የተሰማሩ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ከተሞችን ጽዱ፣ ውብ እና አረንጓዴ በማድረግ ትልቅ አሻራ ማሳረፋቸውን ገልጸዋል። ከዚህ ባሻገር የሥራ ባሕላቸውን በማሳደግ፣ ያገኙትን ዕውቀት እና ክህሎት በተግባር ላይ በማዋል ላሳዩት ጥረትም ምሥጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከነዳጅ ጥገኝነት ከማላቀቅ ባለፈ የድምጽ ብክነትን ያስቀራሉ።
Next articleየ2018/2019 የመኸር ምርትን ስኬታማ ለማድረግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች እየቀረቡ ነው።