
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ እና ለችግር የተጋለጡ 30 ሕጻናትን ተንከባክቦ ለማሳደግ ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ላይ ተረክቧል።
ርክክብ ከተደረገላቸው ሕጻናት ወላጆች መካከል አንደኛዋ እናት በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ ኾነው ልጃቸውን እያሳደጉ እንደነበር ነግረውናል።
ቀደም ሲልም በሌሎች ሰዎች መኖሪያ ቤት አጋዥ ኹነው ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። አሁን ላይ የቤት ኪራይ መክፈል በመቸገራቸው ከከተማ ወጣ ብለው መብራት እና ውኃ የሌለው ቤት ላይ ለመኖር መገደዳቸውንም ጠቅሰዋል።
ትምህርት በሚጀመርበት ወቅት ለሰባት ዓመት ልጃቸው የትምህርት ቁሳቁስ ከረጅ ድርጅቶች ድጋፍ ለማግኘት መመዝገቡን የሰማው ሕጻን “እማየ እኛ ድሀ ነን” በማለት ከፍቶት እናቱን የጠየቃቸው ጥያቄ በእናት አዕምሮ ዛሬም እንዳልጠፋ ተናግረዋል። ዛሬ ግን ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ልጃቸው ለቁምነገር እስኪደርስ ለማገዝ ውል በመውሰዱ ደስታ እንደፈጠረላቸው ነው የገለጹልን።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሴቶች እና ማኅበራዊ አካቶ ሥራ አሥፈጻሚ አልማዝ መሠረት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር እና ምርምር ሥራዎች ባሻገር በማኅበረሰብ አገልግሎት ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ኤች አይ ቪ ኤድስን ቀድሞ መከላከል እና እንዳይዛመት ማድረግ መኾኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል ከ50 በላይ ሕጻናትን ይዞ በቋሚነት እያገዘ እንደኾነም ጠቅሰዋል። ዛሬ ደግሞ ከነበሩት ተጨማሪ 30 ሕጻናትን ለማገዝ እና ብቁ አድርጎ ከራሳቸው አልፎ ሀገርን እንዲጠቅሙ ለማድረግ ከጤና ቢሮ መረከቡን ገልጸዋል።
ትውልድ ስለኾነ የሚተካው ሌሎች ተቋማትም የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲን አርዓያነት ተከትለው ሕጻናትን ተረክበው ለቁም ነገር እንዲያበቁ አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ተወካይ ዳይሬክተር ዓለማየሁ አሠፋ የተቋማት ሠራተኞች እና ደንበኞች ኤች አይ ቪ ኤድስን መከላከል ላይ ዕውቀት እንዲኖራቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከዚህ ባሻገር የኤች አይ ቪ ኤድስ ፈንድ እንዲደራጅ በማድረግ ተቋማት ልጆችን ይዘው እንዲደግፉ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ጠቅሰዋል።
በክልሉ የሚገኙ ተቋማት የኅብረተሰቡ አንድ አካል ስለኾኑ ለችግር የተጋለጡ ሕጻናትን ይዘው እንዲደግፋ ይጠበቃል ብለዋል። ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ 30 ሕጻናትን በቋሚነት ይዞ እንዲደግፍ ለማድረግ ዛሬ የስምምነት ሰነድ መረካከባቸውን ጠቅሰዋል።
የአካባቢ ሀብትን መሠረት ያደረገ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል ሥራ ከተቋማት ይጠበቃል ነው ያሉት። የክልሉ ጤና ቢሮም ይህንን መሠረት ያደረገ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት። በቀጣይም እያንዳንዱ ተቋም ከሠራተኞቹ ጋር ውይይት በማድረግ እና በፈቃደኝነት የኤች አይ ቪ ኤድስ ፈንድን በማጠናከር የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
