ወቅታዊ ሁኔታዎችን ለመሻገር በአንድነት መቆም ይገባል።

10

 

ደብረታቦር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን በወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መሠረት በላይ በዞኑ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የሚዳስስ የመነሻ ሰነድ አቅርበዋል።

በሰነዳቸውም አካባቢው ካጋጠመው ቀውስ እንዲወጣ የመሪዎችን አቅም የመገንባት እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት የመሥራት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

እውነተኛ የሕዝብ ጥያቄን የሚያዳፍኑ እና ክልሉን ከግጭት አዙሪት እንዳይወጣ የሚጥሩ አካላትን በጋራ መታገል እንደሚገባም አመላክተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የመንግሥት ሠራተኞች የሕግ ማስከበር ሥራው ውጤታማ እንዲኾን ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል።

በተለይም በየመንገዱ እና በየኬላው እገታ እና ዝርፊያ በሚፈጽሙ አካላት ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንዲወሰድ፤ የዜጎች የመንቀሳቀስ እና የመሥራት መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ሰላም ለሰው ልጅ ሕልውና መሠረት መኾኑን ገልጸዋል።
በዞኑ ሰላምን ለማስፈን ሰፊ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

የጠላት ኀይሎች በሰው እና በቁሳዊ ሀብት ላይ ጉዳት ለማድረስ ያደረጉትን ሙከራ በእልህ አስጨራሽ ትግል መመከት መቻሉንም ገልጸዋል።

ወደ ነበረው ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል። አንድነት እና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አብራርተዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች ከሐሰት እና ከጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በመውጣት ለሰላም ግንባታ መረባረብ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር) የታሪክ ጠላቶች አጀንዳን በማንገብ ሀገርን ወደ ቀውስ የሚገፉ አካላትን እኩይ ሴራ በአግባቡ የመረዳት እና ለሕዝብ የማስረዳት ኀላፊነት የመንግሥት ሠራተኞች መኾኑን ገልጸዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ሰዓትን በማክበር ለሕዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እና ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሰላም ግንባታ ዕውነትን፣ ሰላምን እና ፍትሕን ማስተማር ከሚዲያዎች ይጠበቃል።
Next articleበነዳጅ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ይፋ ኾኑ።