
ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከዲ ኤስ ደብሊው ኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመኾን ከሚዲያ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዘላለም አረጋ ሚዲያ ለሰላም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ጉልህ መኾኑን ተናግረዋል። የዴሞክራሲ ሥርዓትን በማጽናት የሀገርን ሰላም ለማረጋጋት ሚዲያ ትልቅ ሚና እንዳለው ነው የገለጹት።
ሚዲያ በአግባቡ ካልተመራ ደግሞ አደገኛ መኾኑን
አንስተዋል። አሁን ላይ ደግሞ ሚዲያን በአግባቡ እና በጥንቃቄ መጠቀም አስፈላጊ በመኾኑ የዛሬው ምክክር አሥፈላጊ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ተወካይ ኢሳያስ ገብረ ሚካኤል ለሰላም ግንባታ ዕውነትን፣ ሰላምን እና ፍትሕን ማስተማር ከሚዲያዎች እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በሚዲያዎች ዕውነት፣ ሰላም እና ፍትሕ መስበክ ከተቻለ እንደ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር መቅረፍ ይቻላል ነው ያሉት።
ኀላፊነት በጎደላቸው ሚዲያዎች የሚተላለፉ የተዛቡ መልዕክቶች እና የሀሰት ትርክቶች ወጣቶችን ወደ አልተፈለገ ተግባር እንዲገቡ ስለሚያደርጉ ይህን የሚቀለብስ ኀላፊነት የሚሰማው ሚዲያ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም በሰለም ግንባታ ላይ ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ምክክር ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን ነው የጠቀሱት።
የዲ ኤስ ደብሊው ኢትዮጰያ ካንትሪ ዳይሬክተር ፈየራ አሰፋ ድርጅቱ ለረጅም ዓመታት በወጣቶች የሰላም ግንባታ ዙሪያ ሢሠራ መቆየቱን አንስተዋል። ወጣቶች በግጭት ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት የሚደርስባቸው በመኾኑ የሰላም አሸናፊዎች ለማድረግ እየሠራ መኾኑን አንስተዋል።
ሚዲያዎች ትክክለኛ እና ያልተዛቡ መረጃዎች በማድረስ በኩል ድርሻቸው ጉልህ መኾኑንም አንስተዋል። ወጣቶችን የልማት ባለቤት እና የሰላም አምባሳር ለማድረግ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ኘሬዝዳት አማረ ደጉ ሀሠተኛ መረጃዎች ሀገርን የሚያናጉ እና ለግጭት የሚዳርጉ በመኾናቸው ትክክለኛ የመረጃ ምንጮችን መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ወጣቶች ከስሜት በፀዳ መንገድ የሰላም አምባሳደር መኾን እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የውይይቱ ተሳታፊ የአሚኮ ጋዜጠኛ ትርሲት አሰፋ ሚዲያዎች የሰላም ጋዜጠኝነትን ሊተገብሩ እንደሚገባ ተናግረዋል። በመንግሥት እና በሕዝብ መካካል ድልድይ በመኾን ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት። በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሕዝብን ለአደጋ የሚጥሉ መረጃዎችን ከማሰራጨት መቆጠብ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
የሚዲያ አካላት ገለልተኛ ኾነው ለሰላም እና ለልማት ግንባታ መሥራት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
