
ደብረብርሃን: መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ ሰላድንጋይ ከተማ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም፣ በልማት እና በምርጫ ዝግጅት ዙሪያ የሕዝብ ውይይት ተካሂዷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ሰላም ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ ምርታማ መሬት ያለን እና ልማት ፈላጊ ሕዝቦች በመኾናችን ከጥፋት ይልቅ ልማትን እንመርጣለን ነው ያሉት። ሰላምን ለማስከበር ከመንግሥት ጎን ለመቆም ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ምርጫ ሀገርን የማጽናት እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አካል መኾኑን በመረዳት የምርጫ ካርድ በማውጣት ድምጽ የሚሰጥበትን ቀን በጉጉት እየተጠባበቁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የሚበጀንን በካርዳችን ለመወሰን ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።
የሞጃና ወደራ ወረዳ አሥተዳዳሪ የማነ ብርሃን ተስፋ የሰላም በረከቱ ብዙ መኾኑን ጠቅሰዋል። አካባቢውን ለማልማት ሰላምን መጠበቅ ቀዳሚ ተግባር ሊኾን እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ የሰላም እጦት ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዳያገኙ እና አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ ገበያ እንዳያወጡ እንቅፋት መኾኑን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ ያለውን የአርበኝነት ታሪክ ለሰላም ግንባታ ሊያውለው እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሥልጣን በጉልበት ሳይኾን በሕዝብ ድምጽ ብቻ የሚገኝ መኾኑን መረዳት ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ መኾኑን አስገንዝበዋል።
እያንዳንዱ ዜጋ ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ በነፃነት በመምረጥ መብቱን እንዲያስከብር እና ጥያቄዎቹንም በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያንጸባርቅ አሳስበዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹም አብደታ የሰላድንጋይ ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል። ሀገርን በማጽናት ረገድ የሚታየው አጋዥ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
