
እንጅባራ: መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት እየተሰጠ ይገኛል።
ፖሊዮ የእጅ እና የእግር ሽባነትን በማስከተል ሕጻናትን ለሞት እና ለዘላቂ የአካል ጉዳት የሚዳርግ በሽታ ነው። በሽታው የሚያደርሰውን ጉዳት ቀድሞ ለመከላከልም በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት ክትባት መሰጠት ተጀምሯል።
በክትባት ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፍት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘለቀ ከፋለ የነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናትን ተንከባክቦ እና ጤናቸውን ጠብቆ ማሳደግ የሁሉም ማኅበረሰብ ኀላፊነት መኾኑን ተናግረዋል።
በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር ለተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው ስኬታማነት ኀላፊነት ወስዶ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አሕመድ ሁሴን የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) በሽታ አደገኛ እና ገዳይ በሽታ መኾኑን ተናግረዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሚሰጠው የአምሰተኛ ዙር ክትባት ከ210 ሺህ በላይ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናትን ተደራሽ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
ክትባቱን ለማስፈፀም ከ1ሺህ 400 በላይ ባለሙያዎች እና አስተባባሪዎች ተመድበዋል ነው ያሉት። ክትባቱ ከመጋቢት 18/2018 ዓ.ም እሰከ መጋቢት 21/2018 ዓ.ም ድረስ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
ቤት ለቤት በሚሰጠው በዚህ ክትባት ወላጆች እና አሳዳጊዎች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ልጆቻቸውን ተከታትለው በማስከተብ ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎችም ልጅቻቸውን ተከታትለው በማስከተብ ጤንነታቸውን ለመጠበቅ ቁርጠኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
