በደቡብ ጎንደር ዞን በታጣቂዎች የደረሰውን ውድመት ወደነበረበት ለመመለስ እየተሠራ ነው።

5

 

ደብረ ታቦር: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን እና በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር በታጣቂ ኀይሎች በተለያዩ የልማት ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት እና የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴ ከፍተኛ የክልል የሥራ ኀላፊዎች ተመልክተዋል።

በምልከታው የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ፣ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ እና ሌሎች የክልል እና የዞን ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።

የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት እጅግ አሳዛኝ መኾኑን ገልጸዋል። “ለሕዝብ እታገላለሁ” የሚል ኀይል ሕዝብ በድህነት አቅሙ የገነባቸውን መሠረተ ልማቶች ማውደሙ የጭካኔ ተግባር መኾኑን ገልጸው የደረሰውን ጉዳት ወደነበረበት ለመመለስ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመኾን በቁጭት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ብርቱ ጥረት እየተደረገ መኾኑን አመልክተዋል።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ በዞኑ እና በከተማ አሥተዳደሩ የሕዝብ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረጉ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ዞኑ እና ከተማ አሥተዳደሩ መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ መኾኑንም በምልከታቸው እንዳረጋገጡ ነው የጠቀሱት።

የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ የሚረዳው የሞሰብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የደረሰውን ውድመት መንግሥት በአጭር ጊዜ ለመመለስ ከሕዝብ ጋር በመኾን ምላሽ ለመስጠት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

በኀይል የሚመለስ የሕዝብ ጥያቄ አለመኖሩን ገልጸው ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አሁንም የመንግሥት እጅ እንዳልታጠፈ አረጋግጠዋል።

መጭውን ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ለማከናወን እና ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር መንግሥት የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

ኀላፊዎቹ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ቀና ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ማላቦ ኢኳቶሪያል ጊኒ ገቡ።