
ፍኖተ ሰላም: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም(አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ”የምንገነባው ሕጋዊ እና ሕዝባዊ መንግሥት የሚወሰነው በምርጫ በምናደርገው ተሳትፎ ልክ ነው” በሚል መሪ መልዕክት ከፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ተወያይተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች የውጭ ሀገር ጠላቶች አጀንዳን የሚያሥፈጽሙ አካላትን በቁርጠኝነት ለመታገል መነሳት ይገባል ብለዋል። ሕዝቡን ለምሬት እየዳረጉ ያሉ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ እና ሀገርን ሊያሻግር የሚችል ፓርቲ እንዲመረጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። በምርጫው ሁሉም በንቃት መሳተፍ አለበት ብለዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ ባለፉት ዓመታት በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት በዞኑ በሁለንተናዊ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
የጸጥታ ችግሩ ከፍተኛ ጫና ቢያደርግም የልማት ሥራዎች ግን መከናወናቸውን አንስተዋል። የቀጣዩ ምርጫ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶችን እኩይ አላማ የሚያከስም በመኾኑ ለምርጫው መሳካት ሁሉም መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
አካባቢው ከጸጥታ ችግር ተላቅቆ የሰላም አየር እንዲተነፍስ እና የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በጋራ መረባረብ ይገባልም ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የማኅበረሰቡን እሴት የሚሸረሽሩ እና ትውልዱ ላይ ቁርሾ የሚያኖሩ አካላትን ኅብረተሰቡ መታገል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ኅብረተሰቡን ለከፋ ምሬት እየዳረጉ ያሉ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት መንግሥት እየወሰደ ላለው እርምጃ ተባባሪ መኾን ያስፈልጋል ነው ያሉት። የጸጥታ ችግሩ ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለሰላም ሁልጊዜም መትጋት ይጠይቃልም ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ዞኑ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል። በዚህም የልማት ሥራዎችን በተፈለገው ልክ ማከናወን አለመቻሉን አንስተዋል።
ምርጫ ለአንድ ሀገር የሥልጡን ማኅበረሰብ መገለጫ ነው፤ በስኬት እንዲጠናቀቅም ኅብረተሰቡ ርብርብ ማድረግ አለበት ብለዋል።
ዞኑ የበርካታ ጸጋዎች ባለቤት ቢኾንም በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ሃብቱን መጠቀም አለመቻሉን ነው የገለጹት። ለሰላም መሥራት የአፍራሽ ኃይሎችን እኩይ አላማ ማምከን ነው ብለዋል። ለዚህም በባለቤትነት መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
