ቅድሚያ ለሰላም እንዲሰጥ አባታዊ ሚናቸውን እንደሚወጡ የወልድያ ከተማ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

2

 

ባሕር ዳር (መጋቢት 16/2018 ዓ.ም) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ከወልድያ ከተማ የሃይማኖት አባቶች ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶች በሃይማኖት ተቋማት ሰላም እና ፍቅር እንደሚሰበክ አንስተዋል። ሰው ከራሱ ጋር እንዲታረቅ በዘወትር እንቅስቃሴያቸው ቅድሚያ ለሰላም እንዲሰጡ እያስተማሩ መኾኑን ተናግረዋል።

አማኞች ሰላምን ከሚያደፈርሱ ተግባራት እንዲርቁ እና ሰላምን እንዲያጸኑ እያስተማሩ መኾኑንም ገልጸዋል።
በአንድነት ሰለ ሰላም መጸለይ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

በከፋፋይ እሳቤ እና በግጭት ምክንያት ማኅበረሰቡ ተደጋጋሚ ችግር እያጋጠመው መኾኑንም አመላክተዋል። ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ እና ቅድሚያ ለሰላም እንዲሰጥ የሃይማኖት አባቶች አባታዊ ግዴታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

ሰላምን ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

የወልዲያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ የሃይማኖት አባቶች ግጭቶችን በማስቆም እና ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ በማድረግ ሰላምን ለማጽናት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መኾናቸውን ገልጸዋል። የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የሀገርን አንድነት እና ሰላምን ለማስጠበቅ የሃይማኖት አባቶች ጉልህ ሚና እየተወጡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች የከተማዋን የልማት እንቅስቃሴ እየደገፉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአማራ ባንክ እና ቪዛ ኩባንያ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ለማዘመን ስልታዊ አጋርነት መሠረቱ።
Next articleሀረር በሹዋሊድ በዓል ዋዜማ…