ነዳጅን በቁጠባ እና በአግባቡ እየተጠቀምን ነው።

10
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ በዓለም ላይ የነዳጅ እጥረት እንዳይከሰት ሀገራት የተለያዩ አሠራሮችን እየተገበሩ ይገኛሉ። የአካባቢው ቀጣና ወደተለመደው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እስኪመለስ ነዳጅን በቁጠባ መጠቅምን ኢትዮጵያ እንደ መፍትሔ እርምጃ ወስዳለች።
አሚኮ በወልድያ ከተማ ምልከታ አድርጓል። አሚኮ ያነጋጋራቸው አሽከርካሪዎች ሀገራዊ መልዕክቶችን ታሳቢ አድርገው በታማኝነት ነዳጅ በመቅዳት፤ ተራ አስከባሪዎችን በማክበር እና አለአግባብ በተጠቃሚዎች ላይ ዋጋ ባለመጨመር ችግሩ በዘላቂነት እስኪፈታ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አንስተዋል። ማደያ ላይ ብቻ ነዳጅ እንደሚቀዱም ተናግረዋል።
ወቅቱን በመተሳሰብ እና በመደጋገፍ ማለፍ እንደሚገባም አሳስበዋል። ስግብግብነት እና ያለአግባብ ለመክበር የሚደረግ ጥረትን በማስቀረት ሕዝብን በታማኝነት ማገልገል ያስፈልጋል ነው ያሉት። በታማኝነት ሕዝቡን እያገለገሉ መኾኑንም ተናግረዋል።
የነዳጅ ማደያ ሥራ አሥኪያጆችም ነዳጅ እና ቤንዚን ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎችን ከመንግሥት በተሰጣቸው ኩፐን መሠረት በአግባቡ እያስተናገዱ መኾኑን ተናግረዋል። የጥቁር ገቢያ መቆሙ ኹሉም በአግባቡ እንዲስተናገድ አድርጓል ነው ያሉት።
ቁጥጥሩ የማደያ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ እንዲኾን አስችሏልም ብለዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወንድሙ በከተማዋ አምስት የነዳጅ ማደያዎች መኖራቸውን አንስተዋል። ነዳጅን በቁጠባ ለመጠቀም ቁጥጥር እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
ለአምቡላንሶች፤ ለጸጥታ አካላት እና ለሕዝብ ተሽከርካሬዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥም አንስተዋል።
በከተማዋ ሕገወጥ የነዳጅ ግብይትን ማስቀረት ተችሏልም ብለዋል። ከ15 እስከ 20 ሺህ ሊትር ነዳጅ በማደያዎች በማስቀመጥ ለአደጋ ጊዜ ተቀማጭ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
በከተማዋ የነዳጅ ግብይት በቁጠባ እና በአግባቡ በቁጥጥር እየተመራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። በነዳጅ ምክንያት የተቋረጠ የመሠረተ ልማት ግንባታም ኾነ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንደሌለም ተናግረዋል።
መናኸሪያ አካባቢ የሕዝብ ትራንስፖርት እንዳይስተጓጎል በፍትሐዊነት እና በቁጥጥር ተደራሽ ለማድረግ ከመንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ መምሪያ ጋር በመተባበር እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በጀሪካን ነዳጅ እንዳይቀዳ መደረጉን ተናግረዋል። ሕገ ወጥ የነዳጅ እና የቤንዚን ንግድን ለመቆጣጠር በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ሥራውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ መኖር ለነዳጅ ቁጠባ አማራጭ መንገዶች መኾናቸውን አንስተዋል። በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ በከተማዋ ለ15 ቀናት ለነዋሪዎች ነጻ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።
የነዳጅ ቁጠባውን በተገቢው መንገድ ለመምራት እንዲቻል ማኅበረሰቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም የመፍትሔው አካል እንዲኾንም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበኑሮ ውድነት ላይ ሕገ ወጥ የታሪፍ ጭማሪ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው።
Next article“ጦርነት ሰልችቶናል፤ ሰላም እና ልማት ናፍቆናል” የቋሪት ወረዳ አርሶ አደሮች