ምርጫ ብሔራዊ ጥቅምን እና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ሊኾን ይገባል።

8
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ ሀገራዊ ብሔራዊ ጥቅምን እና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊከናወን እንደሚገባ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የፍልስፍና
መምህር ዓላምነህ አጋጄ ተናግረዋል።
መምህሩ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በምርጫው ሂደት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከምሁራን እና ከዜጎች የሚጠበቁ ግዴታዎች እንዳሉ ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርድን ሕጎች እና ደንቦች በማክበር የምርጫ ቅስቀሳቸውን ማከናወን ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። ፓርቲዎች ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ ከቋንቋ፣ ከብሔር እና ከሃይማኖት ጋር ከሚያያዙ ስሜት ቀስቃሽ ጉዳዮች በመውጣት፣ በራሳቸው ማኒፌስቶ እና በሀገራዊ አንድነት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
“የሌላውን ፓርቲ ክብር መንካት ወይም የተሠሩ በጎ ሥራዎችን ማጠልሸት ለሀገር የሚፈይደው ነገር የለም” ያሉት መምህሩ ፓርቲዎች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ እና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቻቸው ላይ ያላቸውን አማራጭ ሃሳብ ለሕዝቡ በግልጽ ማስረጽ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ገዥው ፓርቲም ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በፍትሐዊ መንገድ የማስተናገድ እና ያላለቁ የልማት ክፍተቶችን ለማረም የመሥራት ኀላፊነት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ምሁራን በምርጫው ሂደት ውስጥ ገለልተኛ ኾነው ሙያዊ ትችቶችን እና አስተያየቶችን በመስጠት ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ አካላት ሃሳቦቻቸውን በሚዲያዎች ለሕዝቡ በማድረስ ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸውም ተናግረዋል። በተለይም ግጭት የሚቀሰቅሱ ንግግሮች አግባብነት እንደሌላቸው ለማስረዳት የምሁራን ምክር አስፈላጊ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የሚዲያ ተቋማትም ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል እና ፍትሐዊ የክርክር መድረኮችን በማመቻቸት ሕዝቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲጨብጥ የማድረግ ኀላፊነት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ እንዲኾን ልዩ ልዩ ማኅበራት ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት። ዜጎችም ነገ ለሀገር ለውጥ ያመጣል፣ ጥቅማችንን ያስከብራል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ በቅድሚያ የመምረጫ ካርድ በማውጣት ዜጋዊ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ማንኛውም ግጭት ለሀገሪቱ ፋይዳ እንደሌለው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡-ሰሎሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጣና ሐይቅን ደኅንነት ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ድርሻ አለበት።
Next articleበኑሮ ውድነት ላይ ሕገ ወጥ የታሪፍ ጭማሪ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው።