
ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የጣና ሐይቅን ከእምቦጭ አረም ለመታደግ በሰው ኅይል እና በማሽን የታገዘ የንቅናቄ ዘመቻ ተጀምሯል።
የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ ጣና ሐይቅ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ኾነ ለሀገር ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ፋይዳ ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የእምቦጭ አረም በሐይቁ ሥነ ምህዳር እና ሕልውና ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኖ መቆየቱን ተናግረዋል። ይህንን ስጋት ለመቅረፍም መንግሥት በበጀት ዓመቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የነበረው የአረም ማስወገድ ሥራ አሁን ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎን ባካተተ መልኩ በንቅናቄ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በአንዳንድ የሐይቁ ዳርቻዎች ቆሞ የነበረው የመከላከል ሥራ በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
የእምቦጭ አረም ባሕሪ በየጊዜው የሚከሰት በመኾኑ የአሁኑ ዘመቻ በአንድ ወቅት ተሠርቶ የሚያበቃ ሳይኾን ቀጣይነት ያለው ክትትል እና ቁጥጥር እንደሚደረግበት አስገንዝበዋል።
በሰው ኀይል እና በማሽን የታገዘውን የአረም ማስወገድ ሥራ ከማጠናከር ባለፈ የሕዝቡን ንቁ ተሳትፎ በላቀ ደረጃ ለማሳደግ እና የተቀናጀ የክትትል ሥርዓት ለመዘርጋት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።
የጣና ሐይቅን ደኅንነት ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኀላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
